የህግ ማስከበር ዘመቻውን በመደገፍ ለሰላምና አንድነት የድርሻችንን እንወጣለን---ተፎካካሪ ፓርቲዎች

139

ደሴ ፣ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ) በደሴ ከተማ የተጀመረውን የመልሶ ግንባታ ልማትና ህግ የማስከበር ዘመቻውን በመደገፍ ለአስተማማኝ ሰላምና አንድነት የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተፎካካሪ ፓርቲዎች አስታወቁ።

የከተማ አስተዳደሩ በልማትና ህግ ማስከበር ዘመቻው ላይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ትናንት ማምሻውን መክሯል።

የኢዜማ ፓርቲ ደሴ ቅርንጫፍ ሊቀመንበር አቶ አይነቱ ሀይሉ በዚህ ጊዜ እንዳሉት፣ ደሴ ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ብትሆንም በሚፈለገው ልክ ባለመልማቷ በኢኮኖሚና በመሰረተ ልማት ወደኋላ ቀርታለች።

ህግ ባለመከበሩ ዜጎች በቀን ጭምር ሲገደሉ፣ሲዘረፉና በሰላም ወጥተው መግባት ሲቸገሩ እንደነበር አስታውሰው፣"ሙስና የተፈቀድ እስኪመስል ድረስ እጅ መንሻ ሲሆን ማየት እየተለመደ መጥቷል" ብለዋል።

ከአሸባሪው ህወሓት ወረራ በኋላ በአዲሱ አመራር የተጀመረው ልማት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ "ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርቲው ከመንግሥት ጎን ሆኖ የሚችለውን ያግዛል" ብለዋል።

"የፓርቲውን አባላትና ደጋፊዎች በማሳተፍ በተለያዩ መንገዶች ለመደገፍ ሁሌም ዝግጁ ነን" ሲሉም አረጋግጠዋል።

መንግስት በቅርቡ የጀመረውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ፓርቲያቸው እንደሚደግፈው ገልጸው፣ ለህግ የበላይነትና ለከተማዋ አስተማማኝ ሰላም በቅንጅት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

"በህግ ማስከበር እርምጃው ንጹሃን እንዳይታሰሩ፣ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችም ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል" ሲሉም አቶ አይነቱ አስገንዝበዋል።

የነፃነትና እኩለነት ፓርቲ ደሴ ቅርንጫፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኪን ፈንታው "የተለያየ የፖለቲካ እሳቤ ብናራምድም በልማት፣ በሰላምና በሀገር ጉዳይ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ያለ ልዩነት እንሰራለን" ብለዋል።

"በተለያየ ምክንያት ለረጅም ጊዜ የተቋረጡና አዳዲስ የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን አሁን በመጀመራቸው ተደስተናል፣ ፕሮጀክቶቹ ፈጥነው ለአገልግሎት እንዲበቁ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ ሰላምና አንድነትም በተግባር እንዲሰፍን ህብረተሰቡና ፓርቲያቸው ሲጠይቅ እንደነበር አስታውሰው፣ የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ በጥንቃቄ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ታጥቆ የሚንቀሳቀስ አካል እየተበራከተ መምጣት በቀጣይ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ስጋት ስለሚሆን መስመር ማስያዝ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ መኪን እንዳሉት ፓርቲያቸው ልማትና ህግ የማስከበር ዘመቻውን በመደገፍ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነው።

"በከተማው የተጀመሩ ልማቶችን እንደገፍለን፤ የድርሻችንንም እንወጣለን" ያሉት ደግሞ የእናት ፓርቲ ደሴ ቅርንጫፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳዊት አያሌው ናቸው።

ህግ የማስከበር ዘመቻው በጥንቃቄና በህገወጥ ተግባራት የተጠረጠሩት ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለበት ጠቁመው፣ ፓርቲያቸው ለሰላም አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል  ተጀምረው የተቋረጡ የመንገድ፣ የድልድይ፣ የመናኸሪያና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ከማስጀመር ባለፈ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በከተማው ወንጀሎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የኅብረተሰቡ የህልውና ጉዳይ ለከፍተኛ ስጋትና አደጋ በመጋለጡ የህግ ማስከበር ዘመቻ መጀመሩን ገልጸዋል።

የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ፣ ሀገር ለማስቀጠልና ጠላትን በተደራጀ አግባብ ለመመከት የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ በጥንቃቄ እየተመራ መሆኑንና በእዚህም ሰላም ማምጣት መቻሉን አስታውቀዋል።

አቶ ሳሙኤል እንዳሉት ቀደም ሲል ህብረተሰቡ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ወንጀለኞችም ለሕግ እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ነበር።

"በአሁኑ ወቅትም ህግ የማስከበር እርምጃውን ደግፎ ከመንግሥት ጎን በመቆም በወንጀል የተጠረጠሩትን አሳልፎ በመስጠትና በመጠቆም የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል" ብለዋል።

የተጀመሩ የልማት ሥራዎችና ህግ የማስከበር ዘመቻው ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከመንግሥት ጎን በመሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጋራ እንዲያስጠብቁ ጠይቀዋል።

በምክክር መድረኩ የተሳተፉት የብልፅግና ፓርቲ፣ እናት ፓርቲ፣ ኢዜማ፣ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲዎች የልማትና የሰላም ሥራዎችን በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ በመድረስ መድረኩ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም