ጃፓን በኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት እቅድ ላይ ትኩረት የተሰጣቸውን ዘርፎች በመለየት ድጋፍ ለማድረግ እየሰራች ነው- አምባሳደር ኢቶ ታካኮ

87

ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ) ጃፓን በኢትዮጵያ የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ላይ ትኩረት የተሰጣቸውን ዘርፎች በመለየት ድጋፍ ለማድረግ እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ፡፡

ጃፓን የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅዱ እንዲሳካ ድጋፍ የምታደርግባቸውን ዘርፎች በሚመለከት ከመንግስት ጋር ውይይት መጀመሩንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የጃፓን መንግስት ከአምስት ዓመት በፊት ለኢትዮጵያ ስለሚያደርገው ድጋፍ እቅድ ማውጣቱን ጠቅሰው፤ አሁን እቅዱን ማሻሻል የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያን ከ2013-2022 ዓ.ም የሚተገበር የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ ነው ያነሱት፡፡

ጃፓን በእቅዱ ላይ የተቀመጡ የልማት ስራዎች እንዲሳኩ የበኩሏን ሚና ለመወጣት እንደምትሻም ተናግረዋል፡፡

ስለሆነም አሁን የድጋፍ እቅዳችንን ከኢትዮጵያ የ10 ዓመት እቅድ ጋር ለማጣጣም እየሰራን ነው፤ በእቅድ ክለሳውም ቅድሚያ ትኩረት የምንሰጣቸውን ጉዳዮች እየለየን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያና ጃፓን የፖሊሲ ውይይት ሲያደርጉ ከስድስት ዓመት ወዲህ የአሁኑ የመጀመሪያ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሯ፤ በቀጣይ ውይይቱ በየዓመቱ እንደሚካሄድ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በዚህም በሚቀጥለው ዓመት ተግባራዊ ለመሆን የተለዩ ፕሮጀክቶችን በሚመለከት መረጃ  ማግኘት እንፈልጋለንም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያና ጃፓን የንግድ ትብብራቸውን እያጠናከሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ኢትዮጵያ ቡና እና አበባን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ጃፓን እየላከች ነው ብለዋል።

በቀጣይም ጃፓን አሁን ያለውን የንግድ ግኑኝነት ወደላቀ ደረጃ የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያና ጃፓን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከርና በተለይም በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በኤዥያ ፓስፊክ ትብብር ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት።

የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሰራ ስለመሆኑም አምባሳደሯ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮም ዘርፉን በከፊል የማዞር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ የጃፓን የቴሌኮም ኩባንያ ገበያውን መቀላቀሉን ጠቅሰዋል።

በዚህም መንግስት ለሳፋሪኮም ከሰጠው ድርሻ ውስጥ የጃፓኑ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን 27 በመቶ ድርሻ ማግኘቱን  ተናግረዋል።

የሱሚቶሙ ኩባንያ ስኬታማ መሆን ሌሎችን የጃፓን ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚስብም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም