በጦርነትና በግጭት አዙሪት ውስጥ እየቀጠልን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ማሻገር ስለማንችል ካለፍንበት የታሪክ ሂደት ልንማር ይገባል

109

ግንቦት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) “በጦርነትና በግጭት አዙሪት ውስጥ እየቀጠልን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ማሻገር አንችልም፤ ካለፍንበት የታሪክ ሂድት ልንማር ይገባል” ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ ገለጹ።

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን ስር የሰደዱ ችግሮች ከጦርነት ይልቅ በውይይት መፍታት የሚቻልበትን አማራጭ የሚፈጥር መንገድ ነው ብለዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ''የሴረኝነትን ሰንኮፍ እንንቀል መተሳሰብና አብሮነትን እንትከል'' በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው ውይይት ዛሬ ተካሄዷል።

የውይይቱ አላማ በቅማንትና አማራ ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት የሚረጋገጥበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ ተገልጿል።

በውይይቱ መድረክ ላይ ዶክተር ዲማ ነገዎ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ስር የሰደዱትን የኢትጵያ ችግሮች ከጦርነት ይልቅ በሰለጠነ መንገድ በመወያያት መፍትሔ ለማምጣት እድል የሚሰጥ አማራጭ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለኮሚሽኑ መጠናከር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

ጠንካራ አገር ለመገንባት ጠንካራና ለማንም ፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኛ ያልሆኑ አገራዊና ሕዝባዊ የሆኑ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም መሬት የወረዱ ሳይንሳዊና በታሪክ የተደገፉ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ የሕዝቦችን አብሮነትና የሰላም እሴቶች የማስቀጠል ኃላፊነት አለባቸው ነው ያሉት ዶክተር ዲማ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ባለፈ ሰላምን ለማምጣት እየተረጉ ያሉ ጥረቶችን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።

በጎንደርና አካባቢው በቅማንትና አማራ ሕዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የሰላም ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን በአብነት ጠቅሰዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአንትሮፖሎጂ መምህር ዶክተር ዳዊት ዮሴፍ የአማራና የቅማንት ሕዝቦች የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና፣ ባህል የታሪክ አውድ ትስስር ከ13ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ነገር ግን የሁለቱ ሕዝቦች ታሪካዊ ትስስር ለመነጣጠል ባለፈው ስርአት በርካታ የፖለቲካ ሴራዎች መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

ሁለቱ ሕዝቦች ዘመናት የተሻገረውን አብሮነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን ሊያስቀጥሉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በውይይቱ ላይ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ በማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪክ ማህበራት አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም