በኦሮሚያ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ 700 ሺህ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ

87

አዳማ፣ ግንቦት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባዎች ለሚገኙ 700 ሺህ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል የክረምት የዜግነት አገልግሎት ማስጀመሪያና የ2015 ዓ.ም የክልሉ የትምህርት ዘርፍ እቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በኦሮሚያ ክልል የቦረናና የምስራቅ ጉጂ እንዲሁም የሐረርጌና የባሌ ቆላማ አካባቢዎች በድርቁ መጠቃታቸውን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።

ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በሚገኙ 700 ሺህ ተማሪዎች ምገባ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ገልጸዋል።

በክልሉ አርብቶ አደር አካባቢዎች ተወስኖ ያለውን የምገባ መርሃ ግብር በሁሉም ዞኖች ለማስፋት መታቀዱን ያመለከቱት ሃላፊው፤ በ2015 ዓ.ም የ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች ምገባ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የ“ቡሳ ጎኖፋ” ተቋም መደራጀቱን ጠቁመው፤ በመርሃ ግብሩ የተካተቱት የቅድመ-መደበኛ እና መደበኛ ተማሪዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

“ተማሪዎች ስለ ምግብ እያሰቡ የሚፈለገውን የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ አይቻልም” ያሉት የትምህርት ቢሮ ኃላፊው፤ የምግብ ተማሪዎች የምገባ አቅምን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

በተያያዘም ከሶስት ሺህ በላይ የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶችና ከ140 በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ሰባት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ስራ መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በኦሮሚያ ክልል በቅድመ-መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ10 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች እየተማሩ እንደሚገኝ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም