በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ6 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዝል በህግ ቁጥጥር ስር ዋለ

115

ዲላ ፣ ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 6 ሺህ 500 ሊትር ቤንዝል ከነተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር መዋሉን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ገለጸ ።

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ብሩ ማርቆስ ለኢዜአ እንዳሉት ትላንት ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በቁጥጥር ስር የዋለው ቤንዝል ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ፖሊስ  ባደረገው ክትትል ነው።

የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 አ/አ B 28951 በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ በህገወጥ መልኩ በ23 በርሜሎች 6 ሺህ 500 ሊትር ቤንዝል ጭኖ ከዲላ ከተማ ወደ ምዕራብ ጉጂ ዞን ሲጓጓዝ እንደነበር ጠቅሰዋል።

አሽከርካሪውም በወንጀሉ ተጠርጥሮ በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።

በህገወጥ መንገድ ነዳጅ እንዲዘዋወር ተባባሪ የሆነው የነዳጅ ማደያን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ምስጋና በራሶ ናቸው።

ከአሰራር ውጪ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ነዳጅን የሚያሰራጩ ማደያዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም  አሳስበዋል።

መንግስት በከፍተኛ ድጎማ የሚያቀርባቸው የነዳጅ ምርቶች በህገወጥ መንገድ በማዘዋወር ሰው ሰራሽ እጥረቶች ከመፍጠር ባለፈ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል ።


ችግሩ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዜጎች ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን ህገወጦችን በማጋለጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል ።