ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው፣ ተፅእኖ ፈጣሪና ሞጋች ትውልድ ለማፍራት የወጣቱን የንባብ ልምድ ማሳደግ ይገባል

225

ጂንካ ግንቦት 19/2014/ኢዜአ/ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለውና በዕውቀት የበለፀገ ተፅእኖ ፈጣሪና ሞጋች ትውልድ ለማፍራት የወጣቱን የንባብ ልምድ ማሳደግ እንደሚገባ የጂንካ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

እንደ ሀገር የንባብ ልምድን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች የሚበረታቱና በየአካባቢው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቋንቋና ስነ-ጥበብ ባለሙያ ወጣት ጆርጅ ጌታቸው እንደገለፀውትምህርት ቤቶች ከመማሪያ መጻህፍት በተጨማሪ ተማሪዎች የታሪክ፣ የስነልቦና፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ፅንሰ-ሀሳብ ያላቸውን መፃሕፍት እንዲያነቡ ማበረታታት እንዳለባቸው ተናግሯል።

የንባብ ክህሎትን ማሳደግ የሚቻለው "ከህፃንነት ዕድሜ ጀምሮ ነው" የሚለው ወጣቱ፤  ወላጆች ልጆቻቸው እንዲያነቡ መምከር፣ መፃሕፍትን ገዝቶ መስጠትና ጥሩ አንባቢዎችን በመሸለም ማበረታታት አለባቸው ብሏል፡፡

ታሪኮቻችንን በጥልቀት ማወቅና መረዳት "ወደሚያግባባ ሃሳብ ላይ ያደርሰናል" ያለው ወጣቱ ለዚህም  አንባቢ ትውልድ መፍጠር  ያስፈልጋል ብሏል።

በጂንካ ከተማ በሚገኘው የህዝብ ቤተ-መጻህፍት የምትሰራው ወጣት የውብዳር ሀብታሙ በበኩሏ በከተማው በህዝብ-ቤተ መጻህፍት ውስጥ የሚገለገሉ ወጣቶች ቁጥር ከከተማው ወጣቶች ጋር ሲነፃፀር  አነስተኛ መሆኑን ተናግራለች፡፡

የንባብ ክህሎት ለማሳደግ ወላጆች ልጆቻቸውን ከመማሪያ መፃሕፍት ውጪ ሌሎች መፃሕፍትን በትርፍ ጊዜያቸው እንዲያነቡ ማበረታታት እንዳለባቸውም መክራለች።

በመጻህፍት ሽያጭ የሚተዳደረው የጂንካ ከተማ ነዋሪ ወጣት ምስጋና ካሳ ወጣቱ በትርፍ ሰዓቱ የተለያዩ መፃሕፍትን ቢያነብ በዕውቀት የካበተ፣ ምክንያታዊ እሳቤ ያለውና የወደፊቱን አሻግሮ የሚያይ ብቁ ዜጋ ይሆናል ሲልም መክሯል።

አብዛኞች ወጣቶች "ከንባብ ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይውላሉ" የሚለው ወጣት ምስጋና፤ የወጣቱን የንባብ ልምድ ማዳበር ካልተቻለ የሀገሩን ታሪክ ጠንቅቆ የሚያውቅና የወደፊት ሀገር ተረካቢ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ይቸግራል ሲልም ስጋቱን ተናግሯል።

በመሆኑም ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያሳልፉትን ረጅም ሰዓት ቀንሰው ለንባብ ማዋል እንዳለባቸው መክሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም