የስፓኒሽ ቋንቋን የአፍሪካ ህብረት ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ በማድረግ አህጉሪቷን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ለማስተሳሰር ጥረት እየተደረገ ነው

74

ግንቦት 19/2014/ኢዜአ/ የስፓኒሽ ቋንቋን የአፍሪካ ህብረት ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ በማድረግ አህጉሪቷን ከተቀረው ዓለም ጋር ይበልጥ ለማስተሳሰር ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

“የስፔን የባህልና ቋንቋ” ቀን አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ ተከብሯል።

የኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊ ተወካይ ኦሊቨር ፒንጋኛ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የቋንቋና ባህል ልዩነትን ማክበር ለዓለም ሰላም መሰረት እንደሆነ ተናግረዋል።

የስፓኒሽ ቋንቋ በአምስት አህጉሮች በሚገኙ 20 አገሮች የሥራ ቋንቋ መሆኑን ገልጸው፤ ከ500 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ሕዝብ የአፍ መፍቻ ቋንቋ እንደሆነም አስረድተዋል።

የካሪቢያን፣ ላቲንና መካከለኛው አሜሪካ ሕዝቦች የስፓኒሽ ቋንቋን በመጠቀም ፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብት፣ ሳይንስ፣ ሙዚቃንና ሌሎች የእለት ተለት መስተጋብሮችን እንደሚያከናውኑም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም  በአሜሪካ ጨምሮ በዓለም ላይ በስፋት ከሚነገሩ አራት ቋንቋዎች አንዱ ሲሆን በቴክኖሎጂ፣ መዝናኛ፣ በሥራ ቋንቋ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ቋንቋ በዓለም ሕዝቦች መካከል ተግባቦትን ለመፍጠር ያለውን ተልዕኮ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የስፓኒሽ ቋንቋን የአፍሪካ ህብረት ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ በማድረግ አህጉሪቷን ይበልጥ ለማስተሳሰር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር ማኑኤል ሳላዛር የስፓኒሽ ቋንቋ በዓለም ላይ በሕዝቦች ተግባቦት ያለውን አስተዋጽኦና ድርሻ አብራርተዋል።

የአፍሪካ ህብረት  ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ፣ አረብኛና ፖርቹጊስን የሥራ ቋንቋ አድርጎ እየተጠቀመ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዛሬው የስፔን ባህልና ቋንቋ ቀን መርሃ-ግብር ላይ የስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪ አገር አምባሳደሮችና ሌሎች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ቋንቋና ባህላቸውን አሳይተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 የቋንቋ ቀን እንዲከበር ከወሰነላቸው  ቋንቋዎች አንዱ ስፓኒሽ መሆኑ ይታወቃል፡፡