ባህላዊ እሴቶችን ለሰላም መረጋገጥ መጠቀም ለቱሪዝም እድገቱ ወሳኝ ነው

67

አሶሳ ግንቦት 19 / 2014(ኢዜአ) ባህላዊ እሴቶችን ለሰላም መረጋገጥ በመጠቀም ዘላቂ የቱሪዝም እድገትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

5ኛው ክልላዊ የባህልና ዙምባራ ፊስቲቫል “ብዝሃ ባህል ለዘላቂ ሰላም እና አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በአሶሳ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ባበክር ከሊፋ እንደገለጹት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የክልሉ ህዝቦች ራስን በራስ ማስተዳደር በመቻላቸው ህገመንግስታዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ አስችሏል።

በተለይም የክልሉ ህዝቦች መገለጫዎች የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን በማልማት በኩል የተገኙ ውጤቶች ከፍተኛ ናቸው ብለዋል፡፡

የክልሉን ህዝቦች ጨምሮ የመላውን ኢትዮጵያዊያን ባህላዊ እሴቶች በማልማት የማስተዋወቅና ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ መስራት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የሀገሪቱ ህዝቦች በተለያዩ ምክንያቶች የሚያጋጥሟቸውን ግጭቶችና የሰላም መደፍረስ ችግሮች ለመፍታት ሲጠቀሙባቸው የቆዩ በርካታ ባህላዊ እሴቶች መኖራቸውን  ጠቅሰዋል።

በተለይ ለቱሪዝም ዘርፉ ዘላቂ እድገት የሰላም መደፍረስ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት  ወሳኝ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሪት መስኪያ አብደላ በበኩላቸው ዙምባራ የሙዚቃ መሳሪያ በክልሉ ከሚገኙ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡

የሙዚቃ መሳሪያውን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ቢሮው ጥረት እንደሚደርግም አስታውቀዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳን ጨምሮ የክልል ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች እንግዶች ታድመዋል።

ባህላዊ ፌስቲቫሉ እስከ ግንቦት 21 / 2014 እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡