በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ ከፋፋይ ሴራዎችን ለማክሸፍ እንደ ቀደምት አባቶቻችን በአንድነት መቆም ይገባል

104

ግንቦት 19/2014/ኢዜአ/  በኢትዮጵያ ላይ በውጭ ኃይሎች የሚቃጡትን ከፋፋይ ሴራዎች ለማክሸፍ እንደ ቀደምት አባቶቻችን በአንድነት መቆም ይገባል ሲሉ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ባሳለፈችው ረዥም የአገረ መንግሥትነት ታሪክ ያጋጠሟትን ሁሉ ፈተናዎች ተቋቁማና መንግሥቷን ጠብቃ በአገርነት በመቀጠል በታሪክ ከተጠቀሱት ጥቂት አገራት አንዷ ናት።

በኢትዮጵያ ላይ ከኦቶማን እስከ ግብፅ ከምዕራባውያን እስከ አገር ውስጥ ባንዳዎች ያልዘመተባት ኃይል የለም ይላሉ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ።

ሆኖም ኢትዮጵያውያን ከመሪዎቻቸው ጋር በተባበረ ክንዳቸው የረዥም ጊዜ አገረ መንግሥታቸውንና አገራቸውን ከነክብሯ አስጠብቀዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ሹመት ገለጻ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ገናና ታሪክ ያላቸው አገራት ጠንካራ ሆነው እንዲወጡ የውጭ ጣልቃ ገብነት ሙከራዎችን ለመቋቋም ያደረጉት ሕዝባዊ የአንድነት ትግል ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

በተለይም ኢትዮጵያውያን በመሳፍንት አገዛዝ የተከፋፈለ ደካማ መንግሥት በነበረበት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የግብፅና ሌሎች የወረራ ሙከራዎችን በአስደናቂ ብቃት የመከቱበት ምስጢር የወቅቱ መሪዎች አንድነት የአሸናፊነት ኃይል መሆኑን በመረዳታቸው ነው ይላሉ።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በአውሮፓ እጅ ያልወደቀ አገር ቆጥሮ ማግኘት ቢያስቸግርም ከዚህ ዕጣ ፈንታ ያመለጠች ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗን ፕሮፌሰር ሹመት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አውሮፓውያንን ድል ያደረገችው ሴራውን አስቀድመው የተረዱ መሪዎች ስለነበሯትና ሕዝቡም አብሯቸው ስለተሰለፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቅኝ-ገዥ ኃይሎች የኢትዮጵያን ነጻ አገርነት በኃይል ተሸንፈው  መቀበላቸውን ያነሱት ፕሮፌሰሩ፤ ሆኖም ኢትዮጵያ የእነሱን የወረራና የቅኝ-ገዥነት ሃሳብ በመቀልበሷ አሁንም ጫና እያደረጉባት ነው ብለዋል።

ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሕዝባቸውን በማስተባበር የውጭ ኃይሎችን ጫና መቋቋማቸውን በመጥቀስ፤ በአሁኑ ወቅት ግን በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው መከፋፈልና አገር ጠልነት ለችግር ዳርጎናል ይላሉ።

ላለፉት 50 ዓመታት ከውጭ ያመጣናቸው ርዕዮተ-ዓለማት ኢትዮጵያውያንን የመከፋፈያ መሳሪያ ሆነው ማገልገላቸውን በመጥቀስ፤ ይህም ምዕራባውያን ባዘጋጁልን አገርን የማዳከም ወጥመድ እንድንገባ እንዳደረገን አንስተዋል።

በተለይ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን የማይወዱ እንዲሁም የኢትዮጵያን ገናና ታሪክ የሚያንኳስሱ ኃይሎች ወደ ሥልጣን መምጣታቸው የኢትዮጵያን መዳከም ለሚፈልጉ ኃይሎች አመቺ እንደነበር ጠቅሰዋል።

“ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ሥልጣን ከያዘ ወዲህ  ሕዝቡ በአገሩ ላይ እንዲነሳ ነው ያደረገው፤ ይህ በዓለም ላይ ታይቶ አይታወቅም"  ብለዋል ፕሮፌሰር ሹመት።

ሕዝቡ እርስ በርሱ በጥርጣሬ እንዲተያይ የሚያደርጉ ትርክቶችን በመንዛት አገሪቱ አሁን ለገባችበት ምስቅልቅል እንዳበቋትም ጠቅሰዋል።

ይህም ለአገር ቁምነገር መሥራት የማይችሉ ኃይሎች በሕዝብ መካከል የአንድነት ሳይሆን የጠላትነት ታሪክ እየሰበኩ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ እንዲነግዱ አድርጓቸዋል ብለዋል።

ጥቃቅን ልዩነቶች ላይ በማተኮር አገሪቱ ለውጭ ጠላት ተጋላጭ እንድትሆን ማድረጉንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ሕዝቡ በኋላቀር ልዩነቶች መጋጨቱን አቁሞ አላዋቂዎች የሚፈነጩባትን አገር ከውጭ ኃይሎች ሥጋት ነጻ ሊያወጧት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን አሁን ያለንበት ሁኔታ የማንቂያ ደወላችን መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ እንደ አገር ህልውናችንን ለማረጋገጥና የውጭ ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ አገራችንን መውደድና እንደቀደምት አባቶቻችን አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

መንግሥትም የውጭ ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍና አገርን ከነክብሯ የማስቀጠል ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት መዘንጋት እንደሌለበት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም