ወጣቱ ትውልድ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና እድገት የበከሉን መወጣት አለበት

190

ግንቦት 19/2014/ኢዜአ/ ወጣቱ ትውልድ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና እድገት የበከሉን ሊወጣ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

የሠላም ሚኒስቴር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት መርኃ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ በጥራትና በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግሯል።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታዬ ደንደአ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ ከተሰጡት በርካታ ተግባራትና ኃላፊነቶች ውስጥ ሰላምና አገር ግንባታ ቀዳሚው ነው።

ለዚህም ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን አስቀድሞ የመከላከል አቅምና ፍላጎት እንዲኖር የግንዛቤ ማሳደግና የውይይት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የዜጎች አስተሳሰብ ከሕብረ ብሔራዊ አንድነት አንፃር እንዲጎለብትና መስተጋብሩን በማጠናከር አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለዚህም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት ዘርፍ 'ለአገሬ ባለኝ እውቀትና አቅም ምን ላበርክት' ብሎ መጠየቅ አለበትም ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚያካሂደው የወጣቶች በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት መርኃ ግብር ወጣቱን በአመለካከት፣ በልምድና በባህሪ ለመቅረጽ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።

የአገልግሎቱ ተሳታፊ ወጣቶች ከሚኖሩበት አካባቢ ወደሌላ አካባቢ ተዘዋውረው በጎ-ፈቃደኛ ሆነው ስለሚያገለግሉ የተዛቡ ትርክቶችን የማስወገድ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።  

የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎቱ ወጣቱ የአገር ፍቅሩን እንዲያጎለብትና ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መደላድል የሚፈጥር መሆኑንም ነው ያስረዱት።

በመርኃ ግብሩ እስካሁን በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንና በእስካሁኑ በተሠሩት ሥራዎች አመርቂ ውጤት መመዘገቡንም ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የኅብረተሰቡ ባህል መሆን አለበት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አገልግሎቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል መመሪያ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ካላቸው ጊዜ፣ ገንዘብ፣ እውቀትና ልምድ በማካፈል አገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት መርኃ ግብር ዓላማ ኢትዮጵያዊ እሴቶችንና መርሆችን ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ የወጣቶችን የአገር ፍቅር፣ ምክንያታዊነት እንዲሁም የሥራ ባህል በማጎልበት አገራዊ አንድነትን በማስፈን ብሄራዊ መግባባትን ማጠናከር መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም