አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት እየተሰራ ነው

382

ግንቦት 19/2014(ኢዜአ) አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ አገር በቀል ቴክኖሎጂ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግርና ፖሊሲ ላይ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አውደ-ጥናት አካሂዷል።     

በአውደ-ጥናቱ ላይ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአገር በቀል ቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶችና ሌሎች  እንግዶች ተሳትፈዋል።  

አውደ-ጥናቱ አገር በቀል የፈጠራ እንዲሁም ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችና የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ እንደተናገሩት፤ በመስኩ ፈጠራን በማበረታታት ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችሉ አሰራሮች እየተዘረጉ ነው።   

አገር በቀል ቴክኖሎጂዎች በጥናትና ምርምር በመደገፍ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ብቻውን ሰርቶ ውጤታማ መሆን እንደማይችል የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በመሆኑም የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ኢንዱስትሪዎች፣የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የምርምርና ኢኖቬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ጄነራል ሰላምይሁን አደፍርስ በበኩላቸው፤ አገር በቀል ቴክኖሎጂ ዘርፍን በአግባቡ ለይቶ ድጋፍ ለመስጠት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ሥራ ላይ እንዲውሉ እና  ወደ ገበያ እንዲወጡ የሚያስችል ድጋፍ እየተደረገ ስለመሆኑም አክለዋል።

ከአደይ አግሮ ቴክ ኩባንያ የመጡት አቶ ቴዎድሮስ አባተ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ ዘመናዊ አሳ ማራቢያ ቴክኖሎጂ ይዘው ቀርበዋል።     

በአሁኑ ወቅት ከሃይቆች አሳ በከፍተኛ መጠን እየተሰበሰበ የአሳ ቁጥር እየተመናመነ መሆኑን ገልጸው፤ ቴክኖሎጂው ለዚህ ችግር መፍትሔ ይዞ የመጣ መሆኑን አብራርተዋል።

ቴክኖሎጂው ቦታ የሚፈልግ በመሆኑ ለምርት የሚሆን ቦታ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል።

ሌላው ቴክኖሎጂ አቅራቢ አቶ ታረቀኝ ጀዳ በበኩላቸው፤ ከአሳ፣ ከአዞና ከሰጎን ቆዳ የተሰሩ ቦርሳ፣ ጫማ እና ያለቀላቸው ቆዳዎችን ለእይታ አብቅተዋል።

ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ ምርቶችን ወደ ገበያ ለማውጣት በሂደት ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

የፈጠራ ሀሳቦች መሬት ላይ ወርደው ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲቻል የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡