የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት አሰራሮች ሊፈተሹ ይገባል ተባለ

81
አዲስ አበባ ጳጉሜ 4/2010 ከኢትዮጵያ እድገት ጋር አብሮ የሚሄድ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት አሰራሮች ሊፈተሹ ይገባል ተባለ። ሲፒዩ ኮሌጅ በመደበኛ፣ በቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በማታ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና፣ በዲግሪና ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል። የኮሌጁ ፕሬዝዳንት ዶክተር አበበ ደምሴ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የሰለጠነና በእውቀት የተካነ የሰው ኃይል ከአገሪቱ የእድገት ፍላጎት ጋር ሲነጻጻር አሁንም ገና ነው። ይህንን ዋነኛ የእድገት ማነቆ በዘላቂነት ለማስወገድም በየዘርፉ የአካሄድና የተግባር ፍኖተ ካርታ መፈተሽ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል። ለዚህም የትምህርት ዘርፉን የበለጠ ለማዘመንና ለማስተካከል በብሔራዊ ደረጃ እየተደረገ ያለውን ጥረት በበጎ ጎኑ እንስተዋል። "የአሁኑ ትውልድ ካለፈው ጋር ሲወዳደር በርካታ እድሎች እንዳሉት ሁሉ ተግዳሮቶችም ይገጥሙታል" ያሉት የኮሌጁ ፕሬዝዳንት፤ ዓለም አንድ እየሆነች በመጣችበት በዚህ ጊዜ በዚያ ልክ ተወዳዳሪ መሆንም ወሳኝ ነው ብለዋል። በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት ዶክተር አሉላ ፓንክረስት በበኩላቸው ተመራቂ ተማሪዎች ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያከናወነች ላለው ልማት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሲፒዩ ኮሌጅ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና 469፣ በዲግሪ 240 እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ 148  በአጠቃላይ 857 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው። ኮሌጁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ለአካውንቲንግና ፋይናንስ ተማሪዎች ተጨማሪ ስልጠና በማዘጋጀት በዓለም አቀፍ መስፈርት በሰርተፍኬት አስመርቋል። ሲፒዩ ኮሌጅ በስልጠና ማዕከልነት በ1985ዓ.ም ተመስርቶ በ1994 ወደ ኮሌጅነት በማደግ በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ በአካውንቲንግ፣ በቢዝነስ አስተዳደርና ሌሎች እያሰለጠነ ሲሆን እስካሁንም 29 ሺህ ሙያተኞችን አስመርቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም