የቲቢ በሽታ የመስፋፋት አዝማሚያ እያሳየ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል

93

ግንቦት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቲቢ በሽታ የመስፋፋት አዝማሚያ እያሳየ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ቅዱስ ጴጥሮስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አሳሰበ።


የቅዱስ ጴጥሮስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ’ሪች ኢትዮጵያ’ ጋር በመተባበር የዓለም የቲቢ ቀንን በኢትዮጵያ ለ25ኛ ጊዜ አክብሯል።


ቀኑም ”ቲቢን ለማጥፋት የድርሻችንን እናበርክት፤ህይወትን እንታደግ!” በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ያግዝ ዘንድ የእግር ጉዞ ተደርጓል።


በተጨማሪም በሽሮሜዳ ለአካባቢው ማህበረሰብ የቲቢ በሽታ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።


የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር መታሰቢያ መስፍን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ዓለም ላይ ከፍተኛ የቲቢ በሽታ ተጠቂ ከሆኑ 30 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።


ሕብረተሰቡን በስፋት እያጠቁ ካሉ ተላላፊ በሽታዎች ውስጥ ቲቢ አንዱ መሆኑን ዶክተር መታሰቢያ ገልጸዋል።


ባለፉት ሁለት ዓመታት አብዛኛውን ትኩረት ኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል ላይ በመሆኑ በእነዚህ ዓመታት ቲቢ በሽታ የመጨመር አዝማሚያ አሳይቷል ብለዋል።


በመሆኑም የቲቢ በሽታን ለመከላከል የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።


በሆስፒታሉ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር እና የቲቢ በሽታ ተመራማሪ ዶክተር ሚሊዮን ሞላ በበኩላቸው፤ሕብረተሰቡ ለቲቢ በሽታ አጋላጭ ከሆኑ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብ መክረዋል።


ሕብረተሰቡ የቲቢ በሽታን ለመከላከል መወሰድ በሚገባቸው ጥንቃቄዎች ከመተግበር አንጻር በጣም የመሰላቸት እና የመዘናጋት ሁኔታ እንዳለም አክለዋል።


የቲቢ በሽታን በጤና ተቋማት አስፈላጊውን ሕክምና በመከታተል ማዳን የሚቻል መሆኑን አስታውሰው፤ ካልታከሙት ግን ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ እንደሆነ ተናግረዋል።


ሰዎች የቲቢ በሽታ ምልክቶች በሚያጋጥማቸው ወቅት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ሕክምና ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበው፤ ቅድመ-ጥንቃቄ እንደሚያሻውም መክረዋል።


በኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም 151 ሺህ ሰዎች የቲቢ በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውንና በዓመት 21 ሺህ ሰዎች በቲቢ በሽታ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያሳያል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️