በአረብ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ጉዳዮች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ለማስቻል ጉባኤው በአረቡ ዓለም የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ ከፈተ

ግንቦት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአረብ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን በሰላም ግንባታና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ በአረቡ ዓለም የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ በኳታር መክፈቱን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለኢዜአ እንደገለጹት ጉባኤው በሠላም ግንባታ ፣በአብሮነት እና በመከባበር የጋራ ዕሴቶች ዙሪያ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ለዚህም ሀገራዊና ተቋማዊ ጥንካሬ እንዲፈጠር ከማስቻል አንፃር ከኢትዮጵያ ውጭ አራተኛውንና በአረቡ ዓለም የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ በኳታር ፣ዶሃ ከፍቷል ብለዋል።

ዶሃ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዳራሽ የሁሉንም ቤተ እምነት ከወከሉ የሃይማኖት አባቶችና በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አልይ በተገኙበት ጋር ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ በይፋ መከፈቱን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከዚህ ቀደም በሰሜን አሜሪካ፣ ኬኒያና ሮም ጣልያን የጉባኤውን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መክፈቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም