ለግብርና ልማት ምቹ የሆነ መሬትና የውሃን ሀብትን በማልማት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው — ኢንጂነር አይሻ መሐመድ

109

ድሬዳዋ፣ ግንቦት 18/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያላትን ለም መሬትና የውሃ ሀብት በዘመናዊ አሰራር በማልማት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የመስኖና የቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።

በመስኖና የቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የተመራው የፌደራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን የመስኖ ልማት እንቅስቃሴዎችን ገምግሟል፡፡

የሲቲ ዞን ከጅቡቲ ወደብ በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝና ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃና ለም መሬት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡         

የፌደራል መንግስት ዞኑ ያለውን ሰፊ መሬትና የከርሰ ምድር ውሃ በመስኖ ለማልማት በከፍተኛ መዋእለ ነዋይ የ28 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቆፋሮ፣ የመንገድና የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችን አከናውኗል፡፡

በሲቲ ዞን የተካሄደው የሥራ ጉብኝት ፕሮጀክቶችን ዝግጁ በማድረግ በሚቀጥለው  ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት ያለመ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም በአዲጋላ ወረዳ 4 ሺ ሄክታር መሬትን በመስኖ ለማልማት ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልፀዋል፡፡

ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀትና አዋጪ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሰፊ መሬትን በመስኖ ለማልማት የሚያስችል የውሃና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መኖራቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

ዞኑ አስፈላጊ መሠረተ-ልማቶች የተሟሉለትና ለጅቡቲ ወደብ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ በርካታ ባለሃብቶች በዘርፉ ለመሰማራት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ያላትን የመሬት፣ የውሃና የሰው ሀብትን ከቴክኖሎጂ ጋር አቀናጅቶ በመጠቀም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የስንዴን ምርትን ለውጭ ገበያ በመላክ የብልፅግና ጉዞዋን ዕውን ታደርጋለች” ነው ያሉት፡፡

በጉብኝቱ ላይ የተሣተፉት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን እንዳሉት የተፈጥሮ ሃብቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ከድርቅ አደጋና የኑሮ ውድነት በዘላቂነት ለመላቀቅ ክልሉ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል፡፡

በሲቲ ዞን የመስኖ ልማት ፕሮጀክት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸው በክልሉ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከ847 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በዘንድሮውና በሚቀጥለው ዓመት የማልማት ስራ ይሰራል ብለዋል።

በሲቲ ዞን አዲጋላ ወረዳ ለሚገኙ አርብቶ አደሮች መቶ ሄክታር የተዘጋጀ መሬት በመስጠትና ድጋፍ በማድረግ ወደ ልማት እንዲሻገሩ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡