መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲፋጠን ያሳለፈው ግጭት የማቆም ውሳኔ የሰብዓዊ ድጋፉ እንዲሳለጥ አድርጓል – ተ.መ.ድ

95

አዲስ አበበ፤ ግንቦት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲፋጠን ያሳለፈው ግጭት የማቆም ውሳኔ በትግራይ ብቻ ሳይሆን ግጭት በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲፋጠን አስችሏል ሲል የተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት ገለጸ።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ተጠሪና የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ፤ መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም ያሳለፈው ውሳኔ የሚፈለገውን ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን ግጭት የተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሚደርሰውን ተጨማሪ ሰብዓዊ ድጋፎች በየብስና በአየር ተደራሽ እንዲሆን ሰፊ ዕድል መፍጠሩንም ነው የገለጹት።

ይህም ብቻ ሳይሆን ከትግራይ ጋር በሚዋሰኑ አማራና አፋር ክልሎች ድንበር አካባቢዎች በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን የነፍስ አድን ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሳለጥ እንዳስቻለም ጠቁመዋል።

መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል ያሳለፈው ግጭት የማቆም ውሳኔ በሰሜን ኢትዮጵያ ድጋፍ የሚሹትን ወገኖች ተደራሽ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ውሳኔው በችግር ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቁሳቁሶችን ተደራሽ ለማድረግ ከማስቻሉ ባሻገር ጥሬ ገንዘብና ነዳጅም ለማጓጓዝ እንዳስቻለ አብራርተዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት ተሰብስቦ ወደ ክልሉ የሚገባው ሰብዓዊ ድጋፍ  ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እንሰራለን ብለዋል።