በደቡብ ወሎና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በ”ሕግ ማስከበር ዘመቻው” ከ500 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል


ግንቦት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በ”ሕግ ማስከበር ዘመቻው” ከ500 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኖቹ አስተዳዳሪዎች ገለጹ።


እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች “የተሻለ ሰላም” ማምጣት ተችሏል ብለዋል።


በደቡብ ወሎ ዞን ”ሕግ ማስከበር ዘመቻው” በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 422 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ እንደሚገኝ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን ገልጸዋል።


ግለሰቦቹ በነፍስ ግድያ፣በስርቆት፣በሽብር፣ ከማረሚያ ቤት የጠፉ፣በሕገ -ወጥ ገንዘብና ጦር መሳሪያ ዝውውርና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።


“ብሔርና እምነትን ሽፋን አድርገው የተጀመረውን ዘመቻው ለማደናቀፍና ለአሸባሪው ህወሓት መረጃና ገንዘብ ሊያቀብሉ የነበሩ ግለሰቦችን ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች በመቀናጀት እንዲያዙ ተደርጓል” ብለዋል።


በተያያዘም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን “በሕግ ማስከበር ስራው” 88 ተጠርጣሪ ወንጀለኞች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እንደሚገኝ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ኃይለማርያም ገልጸዋል።


“የዞኑ ሕዝብ በሕግ ማስከበሩ ላይ ተመሳሳይ የሃሳብ አንድነት መያዙን በተለያዩ ህዝባዊ መድረኮች በመግለጽ ላይ ነው” ብለዋል።


“በሕግ ማስከበሩ የተሻለ ሰላም መጥቷል” ያሉት የዞኖቹ አስተዳዳሪዎች ሕብረተሰቡ ለዘመቻው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም