የኢንዱስትሪውን እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች በተደራጀ አግባብ እየተከናወኑ ነው

48

ደብረ ብርሃን፤ግንቦት 18/ 2014 (ኢዜአ)፡ የአምራች እንዱስትሪውን እድገት የሚያረጋግጡ ስራዎች በተደራጀ አግባብ እየተከናወኑ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ አስታወቁ።

”ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ቃል በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ የምክክር መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

ባለፉት ጊዜያት የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ መጠነኛ ጫና ማሳደሩን የገለጹት ሃላፊው፤ የአምራች እንዱስትሪውን እድገት የሚገቱ ማነቆዎችን በመፍታት ዘላቂ የእንዱስትሪ ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።

ኢንቨስትመንት የህግ የበላይነትና ሰላምን የሚፈልግ ዘርፍ ነው ያሉት አቶ ግርማ፤ ይህን ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን በማወያየት ህግና ስርዓትን ለማስከበር እየተሰራ ነው ብለዋል።

May be an image of 10 people, people sitting, people standing and indoor

 የሀገርን ብሎም የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ባለሀብቶች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በኢቨስትመንት ስም መሬት ወስደው ያጠሩ ባለሀብቶች ፈጥነው ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና መሰል ለኢንቨስትመንት ዘርፉ እንቅፍት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

 ባለፉት 45 ቀናት በተደረገ ጥናት 63 አመራሮች ላይ የክልሉ መንግስት እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢ አለ በበኩላቸው በከተማው ከ65 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡና በተለያየ ደረጃ ያሉ 560 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።

”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆ በመፍታት ለዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ባለሀብቶችም የሀገሪቱን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ በገቡት ውል መሰረት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተው፤ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተቀራርቦ በመስራት እንዲፈቱ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በውይይቱ ከ400 በላይ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን መድረኩን የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደርና የአማራ ክልል እንዱስትሪና ፓርኮች ኮርፖሬሽን በትብብር ያዘጋጁት መሆኑ ታውቋል።