ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነት በመክፈል ለሰብዓዊ መብት መከበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

63

ዲላ ግንቦት 18/2014 (ኢዜአ)..ማንኛውም ዜጋ ግብሩን በታማኝነት በመክፈል ለሰብዓዊ መብት መከበር የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን አስገነዘቡ።

ሁለቱን መሰረታዊ ጉዳዮች ተነጣጥሎ ማየት አንዱ በሌላው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ካለመረዳት የሚመነጭ መሆኑም አመላክተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የህግ ምሁራን መካከል የዲላ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲን ቶሎሳ በዳዳ በሰጡት አስተያየት ለሰብዓዊ መብት መከበር ከመንግስት፣ ከፍትህና ከሰብአዊ መብት ተቋማት ባሻገር የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

በተለይ በኢትዮጵያ በግጭቶችና በተለያዩ ሁኔታዎች የሚከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ከመከላከል ጎን ለጎን ግብሩን በታማኝነት በመክፈል መብቱን የሚጠይቅ ዜጋ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

ግብር መክፈል ከዜጎች የሚጠበቅ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ለሰብአዊነት ከለላ የሚሰጥ መሆኑንም መገንዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል።

በመሆኑም ግብሩን በታማኝነት የሚከፍል ማንኛውም ዜጋ ለአገሩ የሚጠበቅበትን አስተዋጾኦ ከማድረጉም ባሻገር ለሰብአዊ መብት መከበር የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አውስተዋል። 

የግብር ስርዓትና ህጉም የዜጎችን ሰብአዊ መብቶችን ማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ተግባራዊ እንዲደረግ መንግስት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዚህ ረገድ ምሁራን ምርምሮችን በማከናወንና ግንዛቤውን ተደራሽ በማድረግ ጉልህ ሚና እንዳላቸውም እንዲሁ።

በሀገሪቱ የግብር ስርዓትና ሰብአዊ መብቶችን ለማቆራኘት ኢትዮጵያ የተፈራረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች እንዳሉ የሚያስረዱት ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ኃይለማርያም በላይ ናቸው።

ሁለቱን መሰረታዊ ጉዳዮች ነጣጥሎ ማየት አንዱ በሌላው ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ካለመረዳት የሚመነጭ መሆኑን በማከል።

የዜጎች ትልቁ መብትና የሃገራችን ተቀዳሚ ጥያቄ የሆነው ሰብአዊነትን ለማስጠበቅ የፋይናንስ አቅም መጎልበት  ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ሃብት የሚገኝበት ዋነኛው መንገድ ደግሞ ግብር በመሰብሰብ ነው ብለዋል።

ግብር በመሰብሰብ የተሻለ ሀብት ሲፈጠር ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር የሚያስችል አቅም እንደሚኖር ገልጸው ሁሉም ዜጋ ግብሩን በታማኝነት በመክፈል ለሰብአዊ መብት መከበር የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር አስቻለው አሻግሬ በበኩላቸው ግብር መክፈልና የሰብአዊ መብት አያያዝ በእጅጉ የተቆራኙ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከ80 በመቶ በላይ የሆነው የአገር ውስጥ ገቢ የሚገኘው በታክስ ከሚሰበሰብ ገቢ መሆኑን ጠቅሰው ግብር ከሌለ ሰብአዊ መብትን ማስከበር እንደማይቻል አስረድተዋል።

ዜጎች የሰብአዊ መብት ጥሰትን ከመጠየፍና ከድርጊቱ ከመቆጠብ ባለፈ ግብራቸውን በታማኝነት በመክፈል ለሰብአዊ መብት መከበር የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በሌላ መልኩ ግብርን በአግባቡ ማስተዳደር ካልተቻለ ሰብአዊ መብትም በቀላሉ ስለሚጣስ በዚህ ረገድ ግብር ስብሳቢ የመንግስት ተቋማት ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አብራርተዋል።

"የታክስ ስርዓትና የሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ 3ኛው አገር አቀፍ የህግ ጥናትና ምርምር ጉባኤ ሰሞኑን  በዲላ ዩኒቨርሲቲ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም