በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት የግሉን ዘርፍ የመሪነት ተሳትፎ ለማጠናከር መንግስት ድጋፍ ያደርጋል

42

ግንቦት 18/2014/ኢዜአ/ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት የግሉን ዘርፍ የመሪነት ተሳትፎ ለማጠናከር በመንግስት በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከተሰማሩ የግሉ ዘርፍ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ እውቀትን በማመንጨትና ከሌሎች በመጋራት የዜጎችን ህይወት ለመቀየር የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ መከለሱን ገልጸዋል።

የፖሊሲው መከለስ በአገር ውስጥ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ የኢኖቬሽን ምህዳር እንዲጠናከርና የልማት ግቦች እንዲሳኩ መሆኑንም ተናግረዋል።

የግሉ ዘርፍና የመንግስት አካላት ኃላፊነታቸውን በመገንዘብ በቅንጅት እንዲሰሩ የሚያግዝና አገራዊ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቴክኖሎጂ ልማትና በኢኖቬሽን የግሉን ዘርፍ ሚና በማሳደግ መሪነቱን ማረጋገጥም ዋነኛ አላማው መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል።

በመሆኑም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት የግሉን ዘርፍ የመሪነት ተሳትፎ ለማጠናከር በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ፖሊሲው ለዘላቂ ልማት ግብ ስኬት እንዲሁም የ2025 የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ የጎላ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

ለውጤታማነቱም መንግስት የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትና መሰረተ-ልማቶችን ለማሟላት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፉ ለአገር እድገት ለሚኖረው አስተዋጽኦ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን የጉባኤው ተሳታፊዎች አንስተዋል።  

የተለያዩ ተቋማትን መረጃዎች ጠብቆ የሚያቆይ ዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል የተሰኘ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተሾመ ወርቁ ቴክኖሎጂ ዓለም ለደረሰችበት ደረጃ ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሙዓለነዋይን ማፍሰስ የአገርን ማክሮ ኢኮኖሚ ለማሳደግ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑም ተመልክቷል።

የመንግስትና የግሉ ዘርፍ  በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ላይ በቅንጅት መሥራት ለአገር እድገት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

የኦርቢት ኸልዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጳዝዮን ቸርነት በበኩላቸው፤ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ የፈጠራ ሥራዎች በአገሪቱ በየዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እያስቻሉ መሆኑን ተናግረዋል።

የሕብረተሰብን ኑሮ በማቅለል የዜጎች ምርታማነት የሚያሳድግ መሆኑን አንስተው፤ በመንግስት እየወጡ ያሉ ፖሊሲዎችና ሕጎች ለዘርፉ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመተግበር ለሚደረገው ጥረት በተለይም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑ ተመልክቷል።