የመጀመሪያው ከተማ አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፈተ

103

ግንቦት 18/2014/ኢዜአ/  የመጀመሪያው ከተማ አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽንና ገበያ ልማት ማዕከል ተከፈተ።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከግንቦት 18 እስከ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ከ22 በላይ የሚሆኑ አምራቾች ይሳተፋሉ ተብሏል።    

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች፣ የተለያዩ የጥራጥሬ ምርቶች፣ ማር፣ ቅመማ ቅመሞችና ሌሎች የግብርና እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለግብይት ቀርቧል።

የእደ-ጥበብና ሸክላ ውጤቶች፣ ባህላዊ አልባሳት እንዲሁም የቆዳ ውጤቶች በባዛሩ ላይ መቅረቡን ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ አላስፈላጊ የግብይት ሰንሰለትን በማስቀረት አምራችና ሸማች በቀጥታ ለማገናኘት ያስችላል።

ሸማቾች የግብርና ምርቶችን በምክንያታዊ ዋጋ እንዲያገኙና ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ይረዳልም ነው ያሉት።  

የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው አሊ በበኩላቸው፤ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።  

ይህም የአምራችና ሸማችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በመጠቆም።  

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ "የኅብረት ሥራ ማኅበራት ግብይት ለሰላምና ለተረጋጋ የገበያ ሥርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም