በከተማ የትራንስፖርት አቅርቦት ላይ የውጭ ባለኃብቶችን ለማሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ ነው

26

ግንቦት 18/2014 (ኢዜአ) በከተማ የትራንስፖርት አቅርቦት ላይ የውጭ ባለኃብቶችን ለማሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ባለኃብቶችን ለማሳተፍ የታቀደው የትራንስፖርት አቅርቦት እጥረቱን ለማቃለል መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በስብሰባው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን የአሥር ወራት እቅድ አፈጻጸም አዳምጧል።

የምክር ቤቱ አባላት በትራንስፖርት እንዲሁም በሎጂስቲክስ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን አንስተዋል።

ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ትራንስፖርት አሰጣጡን ማዘመን፣ የትራፊክ አደጋ፣ የሥነ-ምግባር ችግሮች፣ የትራንስፖርት አቅርቦት ተጠቃሽ ናቸው።    

በተለይም የትራንስፖርት አቅርቦትን በተመለከተ እጥረቱ ለምን መፍትሄ አላገኘም? የሚለው ጉዳይ ተዳሷል።    

ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በሰጡት ማብራሪያ የትራንስፖርት እጥረቱን ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።      

እንደ ሌሎች ኢንቨስትመንት ዘርፎች በከተማ ትራንስፖርት አቅርቦት ላይ የውጭ ባለኃብቶችን ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።  

ባለኃብቶች እንዴት ይገባሉ? ምን አይነት ማበረታቻዎች ሊኖሩ ይገባል? ለሚለው በፖሊሲ የተደገፈ አሰራር ለመዘርጋት እንቅስቃሴ መጀመሩን አብራርተዋል።    

የውጭ ባለኃብቶችን ወደ አገር ውስጥ ለመሳብ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።  

ከዚህ ባሻገርም የትራንስፖርት እጥረቱን ለማቃለል ተጨማሪ 110 አውቶቡሶች በግዥ ሂደት ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል።    

በአገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት 460 ሚሊዮን ሰዎችን ለማጓጓዝ ታቅዶ ለ417 ነጥብ 1 ሚሊዮን ተጓዦች አገልግሎት መስጠት ተችሏል።   

አሁን ላይ ከ10 ሺህ የትራፊክ አደጋዎች መካከል 32 ነጥብ 6 ሰዎች ላይ ጉዳይ ይደርሳል ያሉት ሚኒስትሯ ይህንን ወደ 30 ዝቅ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።  

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከጳጉሜ እስከ ጳጉሜ እንደርሳለን፣ መንገድ ለሰው፣ የእግረኞችና ብስክሌተኞች ቀን በሚሉ መሪ ሃሳቦች የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብሮች ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም አደጋ ይበዛባቸዋል ተብለው የተለዩ ቦታዎች ላይ የመንገድ ምልክቶች፣ የእግረኛ ማቋረጫ ዜብራ ቀለም መቀባትና የፍጥነት መገደቢያዎች እንዲሰሩ ተደርጓል ብለዋል።      

ሚኒስትሯ እንዳብራሩት፣ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በተሰሩ ሥራዎች ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ6 በመቶ መቀነስ ተችሏል።  

በሌላ በኩል የሎጂስቲክስ ወጪን ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ ማዳን እንደተቻለ ተናግረዋል።  

ለአብነት ሲጠቅሱም ወደ ውጭ የሚላከው የቡና ምርት 98 በመቶ በአገር ውስጥ በኮንቴይነር ታሽጎ በመላኩ ሊወጣ የሚችል ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።