በሰሜን ወሎ ዞን የከተሞችን የመሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው

163

ወልዲያ ግንቦት 17/2014 (ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን በከተሞች የሚስተዋለውን የመሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት ከ247 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ መለሰ ተሻለ ለኢዜአ እንዳሉት በህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚነሱ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው።

በዞኑ 77 ፕሮጀክቶችን በመንደፍ በወልዲያ፤ በቆቦ፤ በላልይበላና መርሳ ከተሞች የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች  እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት የፍሳሽ መውረጃ ፣ የኮብልስቶን መንገድ፣ የመንገድ ዳርቻ ግንብ ስራ፣ የጠጠር መንገድ ስራ፣ ዘመናዊ የአነስተኛ ገበያ ሼድ፣ የድልድዮች ግንባታ፣ የመንገድ ጥገና፣የውሃ መስመር ዝርጋታና መሰል ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።

ግንባታዎቹ የህዝቡን የመሰረተ-ልማት ጥያቄ ከመፍታታቸው ባሻገር ለ525 ወገኖች በስራ እድል ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ ከዓለም ባንክ በተገኘ ከ247 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የበጀት ድጋፍ በዘንድሮው ዓመት የተጀመሩ መሆኑን ጠቅሰው እስከ ዓመቱ ማጠናቀቂያ ለአገልግሎት እንዲበቁ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል።

”ተወልጄ ያደግኩበትን ከተማ ለማልማትና አሻራዬን ለማስቀመጥ በመቻሌ እድለኛ ነኝ” ያለችው  ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በስቪል ኢንጂነሪግ ተመርቃ የስራ እድል የተፈጠረላት ወጣት አይናዲስ ዘገዬ ናት።

የተረከቡትን የግንባታ ስራ በጥራትና በወቅቱ አጠናቀው ለማስረከብ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግራለች፡፡

በጌጠኛ ድንጋይ ማንጠፍ ስራ የተሰማራችው ወጣት ሰላማዊት አሻግሬ እንዳለችው “አሁን ያገኘሁት ሥራ እኔንም ሆነ ቤተሰቤን ለማገዝ አስችሎኛል” ብላለች።

እየገነቧቸው ያሉት መንገዶች ለተገልጋዩ ምቹ ከማድረግ ባለፈ የከተማውን ውበት እንዲጨምሩ በማድረግ ሙያዊ ብቃታቸውን ለማስመስከር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሳለች።

የወልዲያ ከተማ ነዋሪ አቶ ደጀኔ ይርሳው እንዳሉት ከተማው በተራራ የተከበበ በመሆኑ ዝናብ ሲዘንብ የሚከሰተው ጎርፍ ቤቶችን እያፈረሰና መንገዶችን እየዘጋ ሲቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል።

አሁን እየተገነቡ ያሉት ደረጃቸውን የጠበቁ የጎርፍ ማፋሰሻ ቦዮች ችግሩን የሚቀርፉልን ናቸው ብለዋል።

የመንገድ ግንባታው ተሸከርካሪ የማያስገቡ መንገዶችን በመክፈት፣ የተበላሹ መንገዶች  በመጠገናቸው ህሙማንና ነፍሰ-ጡሮችን ወደ ህክምና ተቋም በተሽከርካሪ ለመውሰድ የሚያስችልና የህዝብን ጥያቄ የመለሰ ልማት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በከተማው እየተገነቡ ያሉት ድልድዮች ቀበሌን ከቀበሌ ጋር የሚያገናኙ፤ ረጅም ሰዓት የሚወስዱ መንገዶችን  በአቋራጭ ለመጓዝ የሚያስችሉ በመሆናቸው መደሰታቸውን የገለጹት አቶ ገዳሙ አለባቸው ናቸው።