በደቡብ ክልል ከመስኖ ልማት ከ24 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ

105

ወራቤ፤ ግንቦት 17/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በተያዘው ዓመት በተካሄደው የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ ከ24 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቀ።

ቢሮው የ2014 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረኩን በወራቤ ከተማ አካሂዷል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር እንደገለጹት ምርቱ የተሰበሰበው በባህላዊና ዘመናዊ መስኖ ከለማው 234 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ነው።

 ድንች፣አደንጓሬ፣ቦለቄ፣ገብስ፣ስራስራና የአትክልት ምርቶች በመስኖ ከተመረቱት ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰራው ስንዴን በመስኖ የማልማት እንቅስቃሴም ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ለማልማት ታቅዶ 5 ሺህ ሄክታር  መልማቱን ጠቁመዋል።

ከዚሁ የስንዴ የበጋ መስኖ ልማትም ከ 146 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።

ግብርናን ለማዘመንና የባለድርሻ አካላትን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በተደረገው ጥረት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች በበጋ መስኖ ልማት ስራው ያሳዩትን ተነሳሽነትና  ያስመዘገቡትን ውጤት በሌሎች የግብርና ስራዎች ላይ መድገም እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው ዘንድሮ በተካሄደው የበጋ መስኖ ልማት ስራ ከ150 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ማሳተፍ ተችሏል።

የመስኖ ልማቱ ከ52 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ መካሄዱን ጠቁመው፤ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም የቴክኖሎጂና የግብዓት ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

በሁለት ዙር ከተካሄደው የመስኖ ልማት 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት  መቻሉን ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር ስንዴን ከውጭ ለማስገገባት የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለመታደግ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም በዞኑ የተለያዩ ስራዎች መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙርሰል አማን ናቸው።

ከሌሎች የመስኖ ስራዎች በተጓዳኝ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተግባራዊ ለማድረግ በተደረገው ጥረት  ከ3 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 1 ሺህ 100 ሄክታር ማሳ በማልማት 41 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም