በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የትምህርት ተደራሽነት እንዲኖራቸው የባለድርሻ አካላት ርብርብ ተጠየቀ

አዳማ፤ግንቦት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በግጭትና ተፈጥሮ ክስተት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የትምህርት ተደራሽነት እንዲኖራቸው የባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።


ጥራት ያለው ትምህርትን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ያለመና በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዳሚክ ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ኤባ ሚጀና በኮንፈረንሱ መክፈቻ እንዳሉት ጦርነት፣ ግጭትና የተፈጥሮ አደጋዎች ክስተት በቀጠናው በርካታ ዜጎች ጥራት ያለውን ትምህርት እንዳያገኙ መንስኤ ሆኗል።


የኮንፈረንሱ ዓላማ በቀጠናው ውስጥም ሆነ ድንበር ተሻጋሪ ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለማመንጨት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።


በጦርነት፣ በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈናቀሉ ዜጎች ምን ዓይነት ትምህርት በምን መልኩ ማግኘት እንደሚችሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ጭምር መሆኑንም ገልጸዋል።


በተለይ "ህፃናት ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀልና መራቅ የለባቸውም" ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት።


በሀገራችን የሰሜኑ ክፍል በጦርነት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ከበፊቱ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ ተቋማቱን መልሶ የመገንባትና የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ኤባ አንስተዋል።


ከትግራይ ክልል ውጭ የነበሩና በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ መማር ማስተማር መግባታቸውን ለአብነት አንስተዋል።


ኮንፈረንሱ በግጭቶችና በተለያዩ ምክንያቶች ከጎረቤት ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡና ከሀገራችን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተፈናቅለው ያሉ ህፃናትና ዜጎች በምን መልኩ ትምህርት ማግኘት እንደሚችሉም ጭምር የሚመክር ነው ተብሏል።


እንዲሁም አመቺ የሆነ ስርዓተ ትምህርት እንዲኖር ጭምር ለቀጠናው መንግስታት የፖሊሲ ግብዓት ሊሆን የሚችል ምክረ ሃሳብ የሚቀርብበት እንደሆነም አንስተዋል።


በተለይ የተፈናቀሉ ህፃናት በሚችሉት ቋንቋ የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት(ኢጋድ) እገዛ አማራጮች ይቀርባሉ ነው ያሉት።


ኮንፈረንሱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነ ባህሪ ኮሌጅና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በትብብር የተዘጋጀ ሲሆን በኮንፈረንሱ ከአሜሪካ፣ አውሮፓና የአፍሪካ ሀገራት በበይነ መረብ የተለያዩ ምሁራን በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ኮንፈረንሱ ዛሬን ጨምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ መሆኑም ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም