በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት ለሚከናወነው ሀገር አቀፍ የኦሎምፒክ ውድድር በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት ለሚከናወነው ሀገር አቀፍ የኦሎምፒክ ውድድር በቂ ዝግጅት ተደርጓል

ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከግንቦት 21/2014 ጀምሮ ለተከታታይ አስራ አምስት ቀናት ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የኦሎምፒክ ውድድር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የሲዳማ ክልል ፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኋላፊ አቶ ፊሊጶስ ናሆም ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ አዘጋጅነት ለሚደረገው ሀገር አቀፍ የኦሎምፒክ ስፖርቶች ውድድር ስኬት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ዝግጅቶችን ገምግሟል።
ኮሚቴው የስፖርታዊ ውድድሮች የሚደረግባቸውን ሜዳዎች ዝግጅት፣ የስፖርተኞች ማደሪያ ስፍራ፣ የስፖርተኞችን ጤንነት ለመከታተል የሚያስችል ክሊኒክና የህክምና ቁሳቁስ ዝግጅት መገምገሙን ገልጸዋል።ለተወዳዳሪዎቸ በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ለማድረግ ዝቅጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።
ሀገር አቀፍ የኦሎምፒክ ውድድሩ ያለምንብም የጸጥታ ችግር በአስተማማኝ ሰላም እንዲካሄድ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በመጪው ግንቦት 21 በሀዋሳ የሚጀመረው የኦሎምፒክ ውድድር የመክፈቻ በሲዳማ ባህላዊ የቄጣላ ስነስርዓትና በሌሎች ባህላዊ ክዋኔዎች እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
ባህላዊ ዘፈኖች፣ ሰርከስ፣ ቴኩዋንዶና ሌሎች ክዋኔዎች ኦሎምፒኩ በድምቀት እንዲከናወን ይደረጋል ብለዋል፡፡
ሁሉንም ክልሎች ጨምሮ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ የኦሎምፒክ ስፖርታዊ ውድድሮች በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚጀመር አቶ ፊሊጶስ ጠቁመዋል።