ቤልጂየም ኢትዮጵያ ለማካሄድ ያሰበችውን አገራዊ ምክክር ለመደገፍ ዝግጁ ናት

195

ግንቦት 17/2014/ኢዜአ/ ቤልጂየም ኢትዮጵያ ለማካሄድ ያሰበችውን አገራዊ ምክክር ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር ፍራሲዮስ ዱሞንት ገለጹ።

አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሰላም ማስከበር እና የጸጥታ ተልእኮዎች ዋና ተዋናይ ሆና መቆየቷን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ የሚታዩ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዚህም እንድ ሀገር የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።

አምባሳደር ፍራሲዮስ አገራዊ ውይይቱ ስኬታማ ከሆነ ኢትዮጵያውያን በደስታ የሚኖሩባት አገር መገንባት እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።

ለዚህ ደግሞ ቤልጂዬም የአገራዊ ምክክር ሂደቱን የምትደግፍ መሆኑን ነው የተናገሩት።

አምባሳደር ፍራንሲዮስ ቤልጂየምና ኢትዮጵያ ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑንም አስታውሰዋል።

ቤልጂየም ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተሰረቀውን መስቀል መመለሷ የጠንካራ ወዳጅነት ማሳያ መሆኑን እንደ ማሳያ አንስተዋል።

አምባሳደሩ የሁለቱን አገራት የንግድ ግንኙነት አስመልክቶም ኢትዮጵያ እንደ አበባ እና ቡና ያሉ ምርቶችን ወደ ቤልጂየም እንደምትልክ ገልጸዋል።  

ቤልጂየም ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በሁለተኛና እና በሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ በርካታ የነፃ ትምህርት ዕድል መስጠቷንም ጠቅሰዋል።

ቤልጂየም ኢትዮጵያ በ1930ዎቹ የ'ሊግ ኦፍ ኔሽን' አባል እንድትሆን በማመቻቸት ያላሰለሰ ጥረት አድርጋ እንደነበርም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በንጉሱ ዘመን የክቡር ዘብ እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማድረጓንም አንስተዋል።

የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1919 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም