በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው

105

ደሴ፣ ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ ገለፁ።

ዋና አስተዳዳሪው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ህብረተሰቡ ‘የህግ የበላይነት አልተከበርም’ በሚል ጥያቄ ሲነሳ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተገቢው ሁኔታ ህግ ባለመከበሩም ስርቆት፣ ግድያ፣ ዘረፋ፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባሮች የህብረተሰቡን ህይወት አደጋ ላይ ጥሎት መቆየቱን አስታውሰዋል።

ህግ ለማስከበር መንግሥት በቅንጅት በወሰደው እርምጃ በወንጀል የተጠረጠሩ 145 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ መታየት መጀመሩንም ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎችን ለይቶ ለህግ ለማቅረብ በተደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው፤ ንፁሃን ያለአግባብ እንዳይያዙና እንዳይንገላቱ በጥንቃቄ እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተጨባጭ ለውጥ በመምጣቱ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ገልጸዋል።

የህግ ማስከበር እንቅስቃሴው የተሟላ እንዲሆን ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ የጀመረውን የመጠቆም፣ የማጋለጥና አካባቢውን የመጠበቅ ተግባሩን በማጠናከር ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር የጀመረውን ቅንጅት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

May be an image of 1 person and outdoors

ከኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የደዋ ጨፋ ወረዳ ነዋሪ ሸህ እንድሪስ ሸህ ታጁ በሰጡት አስተያየት ህብረተሰቡ ዘመቻውን በመደገፍ በወንጀል የተጠረጠሩትን አሳልፎ ለህግ እየሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል።

አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲከበር ህዝቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ እንደነበረ አስታውሰው፤ ዘመቻውን በማጠናከር የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።