አሸባሪው ህወሃት ለዳግም ጦርነት እያደረገ ያለውን ዝግጅት አለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ሊመለከተው አይገባም

82

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት ለዳግም ጦርነት እያደረገ ያለውን ዝግጅት አለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ሊመለከተው እንደማይገባ በኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የሚታወቁ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ ገለጹ።

በአሜሪካ ለ45 አመታት የኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዳኛቸው ተሾመ፤ በጦርነቱ የወደሙ መሰረተልማቶችን ዳግም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በሰብአዊ ድጋፍና ሌሎች በጎ ስራዎች በመሳተፍ ለአገራቸው በሚችሉት ሁሉ እግዛ ለማድረግ ዝግጁ በመሆን የሚጠቀሱ ግለሰብም ናቸው።

ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት አጋጣሚ ኢዜአ ያነጋገራቸው ዳያስፖራው፤ አሸባሪው ህወሃት በአገርና ህዝብ ላይ ያደረሰው ጥፋት በእጅጉ አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ አሁንም ጥፋት ለመፈፀም ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን በግልጽ እየተናገረ መሆኑን ጠቅሰው አለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ሊመለከተው አይገባም ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በተለይም በትምህርት፣ በጤና እና ሌሎችም የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጥፋት መፈፀሙንና አሁንም ለተመሳሳይ አላማ እየተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል።

የተለያዩ ተቋማትን ብቻ በማውደም ያልቆመው የጥፋት ሃይሉ ዜጎችን በጅምላ በመግደል፣ ሴቶችን በመድፈር፣ ንብረት በመዝረፍና በማቃጠል ጭምር ይቅር የማይባል ጥፋት መፈጸሙን አስታውሰዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በማይካድራ የፈፀመው የጅምላ ጭፍጨፋ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚገባው ልክ አለመወገዙን ጠቅሰው በቆቦ፣ ውጫሌ እንዲሁም በአፋር ጋሊኮማ እና ሌሎችም አካባቢዎች አሰቃቂ ተግባራትን ፈፅሟል ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን አሸባሪ ቡድን አለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ከማለፍ ይልቅ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሔደበት ያለውን ጥረት ሊያግዝ ይገባል ነው ያሉት።

አምንስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በሚያወጡት ሪፖርት የአሸባሪውን እውነታ ከመሸሽ ይልቅ ማጋለጥ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

መንግስት ለሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት ጥረት እያደረገ ቢሆንም አሸባሪው ህወሃት በማስተጓጎልና የደረሰውንም ለራሱ ጥቅም በማዋል የትግራይ ህዝብ ለስቃይ እንዲዳረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የአሸባሪውን ጥፋት በጋራ እንዲያወግዙ ዳያስፖራው ጠይቀዋል።