በጎ እሴትንና ሰላምን በትምህርት ተቋማት ውስጥ በዘላቂነት ለመገንባት ከመምህራን ጋር እየተሰራ ነው

64

ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎ እሴትንና ሰላምን በትምህርት ተቋማት ውስጥ በዘላቂነት ለመገንባት ከመምህራን ጋር እየተሰራ መሆኑን የክልሎች የመምህራን ማህበራት ገለጹ።

የመምህራንን የተጠቃሚነት ጥያቄም ደረጃ በደረጃ በመመለስ መምህራን በትውልድ ቀረጻ ላይ ብቻ ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ልዩ ልዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተመልክቷል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የስርዓተ ጾታ ተጠሪ በዛ ወርቅ ኩማ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የሰላም ግንባታን በትምህርት ማህበረሰቡ ለማስረጽ ከተቋማት፣ ከመምህራንና ከተማሪዎች ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የትምህርቱ መስክ ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም ገልጸው፤ የመምህራንን አቅም በመገንባት ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል መምህራን ማህበር ዋና ጸሐፊ ታደለች ወርቁ በበኩላቸው ሰላም ለትምህርት ስራ ስኬታማነት ትልቅ እንዳለው ተናግረው፤ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ማህበራችን ከትምህርት ቢሮና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ መምህራን ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው አስታውሰው፤ ለሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ መምህራኑ የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ማግኘት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል የመምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት መምህር ለማ ካዬሶ በበኩላቸው ማህበሩ እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅር በማደራጀት ሰላምን በዘላቂነት ለመገንባት እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

ለመምህራን፣ ለሀላፊዎችና ለዘርፉ ተዋንያን የአቅም ግንባታ ስልጠና ከመስጠት ጎን ለጎን የመምህራን ጥቅም እንዲጠበቅም እየተሰራ ነው ብለዋል።

ራቅ ባሉ ከተሞችና ወረዳዎች ባሉ ትምህርት ቤቶችም ተወካዮችን በመሰየም ሰላምን የሚያደፈርሱ ነገሮች እንዳይፈጠሩ የክትትል ስራዎች እየተሰሩ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

የጋምቤላ የመምህራን ማህበር ሂሳብ ሹም እኩኚኝ ካን የግጭት ሀሳቦች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ ግንዛቤ የመፍጠርና በተማሪዎች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር የመከላከል ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

መምህራን ልዩ ልዩ ጥቅማቸው ተከብሮ በሰላምና ስብዕና ግንባታ ላይ እንዲያተኩሩም ማህበራችን እየሰራ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

ትምህርት የእውቀትና የበጎ አመለካከት ቁልፍ መሳሪያ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ፤ በጎ እሴትን ለመገንባትና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመምህራንን ጥያቄ መመለስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ዘመኑን የሚመጥን የመማር አስተማሪያ ግብዓቶችን ለማሟላት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በመላ ሀገሪቱ ከ700 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።