በኦሮሚያ ክልል ግብርናን ከተለመደው አሰራር ለማውጣትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይሰራል

47

ግንቦት 17/2014(ኢዜአ)፡ በኦሮሚያ ክልል ግብርናን ከተለመደው አሰራር በማውጣት በዓመት ሶስት ጊዜ ማምረትና ሜካናይዜሽንን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

ክልሉ የ2014/15 የመኸር ወቅት እርሻን በዘር የመሸፈን ስራ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ በቆሎን በኩታ ገጠም በመዝራት ትናንት  በይፋ አስጀምሯል።  

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ፤ በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት ዝናብን ብቻ በመጠበቅ በዓመት አንድ ጊዜ ከሚካሄድ የተለመደ የግብርና  አሰራር በመውጣት ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ የተጀመረው ሥራ አመርቂ ውጤት ማስገኘት ጀምሯል።

በተለይም በዝናብ ውሃ ጥገኛ የነበረውን የክልሉን ግብርና በመቀየር በዓመት ሶስት ጊዜ የማምረት ስራ እየተለመደ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከሶስቱ የምርት ጊዜያት በመኸር እርሻ  በክልሉ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር ማሳን በዘር ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ  4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ በኩታ ገጠም ታርሶ ለዘር እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።

አርሶ አደሩ “በኩታ ገጠም እርሻ ብቻ የሚፈለገውን ምርት ማምረት አይችልም” ያሉት ምክትል ሃላፊው፤ የሜካናይዜሽን ግብርናን ማሳደግ ወቅቱ የሚጠይቀው መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሳደግ  በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

ከ4 ሺህ በላይ ትራክተሮች ለክልሉ አርሶ አደሮች ተከፋፍለው  ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመው፤ በቅርቡም ተጨማሪ ትራክተሮችን ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዘንድሮው ዓመት የገጠመውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመተካት 42 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ኮምፖስት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የምርጥ ዘርና ግብዓት አቅርቦት ላይ የሚታየውን ክፍተት በመቅረፍ የታቀደውን የ205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተረፈ አራርሳ በበኩላቸው በዞኑ 613 ሺህ ሄክታር ማሳ በኩታ ገጠም ለመዝራት መዘጋጀቱን ገልጸው፤ ከኩታገጠም ባለፈ ኩባንያን ወደመፍጠር ለመሸጋገር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኩታ ገጠም ማረስ በርካታ ጠቀሜታዎችን እንዳስገኘላቸው የሚናገሩት ደግሞ በእለቱ በኩታ ገጠም የእርሻ ስራ ላይ ተሳታፊ የነበሩት አርሶ አደሮቹ ናቸው።

የመኸር የዘር ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ በኖኖ ወረዳ ቢፍቱ ጃለላ ቀበሌ የተጀመረ ሲሆን በኩታ ገጠም ታርሶ የተዘጋጀ 1 ሺህ 35 ሄክታር መሬት በበቆሎ ዘር መሸፈኑ ተመላክቷል።