"የአፍሪካ ወጣቶች አህጉራቸውን ከድህነትና ኋላ ቀርነት ነፃ የሚያወጡ የቃል ኪዳን ልጆች ናቸው"- አቶ ደመቀ መኮንን

118

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ ወጣቶች በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አህጉራቸውን ከድህነትና ኋላ ቀርነት ነፃ የሚያወጡ የቃል ኪዳን ልጆች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

"የፓን አፍሪካ የወጣቶች ስብሰባ 2022" ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ የአፍሪካ ወጣቶች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

አፍሪካውያን የመላው ዓለም ጥቁሮች ኩራትና የነፃነት ቀንዲል ከሆነው ከአድዋ ድል በመማር ራሳቸውን ከምዕራባውያን ቅኝ አገዛዝ ነፃ አውጥተዋል፡፡

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የአሁኑ የአፍሪካ ህብረትን እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1963 በመመስረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገራት የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እንዲጀመር አድርገዋል፡፡

አፍሪካውያን ከምዕራባውያን የቅኝ አገዛዝ ስርዓት በመውጣት በፀጥታ፣ መሰረተ ልማት፣ የኢኮኖሚ ትብብር ላይ በጋራ መስራት ጀምረዋል፡፡

May be an image of 2 people, people sitting, people standing and indoor

ለዚህ አንዱ ማሳያው ደግሞ በፓን አፍሪካኒዝም የወጣቶች ንቅናቄ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚመክር የአፍሪካ ወጣቶች የጋራ ስብሰባ መካሄድ መጀመሩ ነው፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት፤ አፍሪካውያን አባቶቻቸው ለአፍሪካ ነፃነትና ሉዓላዊነት ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡የዚህ ትውልድ ወጣቶች ደግሞ በብዙ መስዋዕትነት ያቆዩልንን ነፃ አህጉር ከድህነትና ኋላ ቀርነት በማላቀቅ ሁለተኛውን የነፃነት ጉዞ መጀመር አለባቸው ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ወጣቶች ሙሉ ጊዜያችሁን ለአፍሪካ አህጉር አንድነት፣ ሰላምና ልማት እንደምታውሉ በእናንተ ተስፋ አለኝ ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋየ ወጣቶች የነገ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ዛሬ ላይም የቀጣዩን ትውልድ መሰረት የሚገነቡ ናቸው ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ወጣቶች ሰላሟ የተረጋገጠባትና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ሀላፊነት የሚሰማቸው ተተኪዎች መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የወጣቶች ፖሊሲ በ2014 ማጽደቋን ገልጸው፤ "በትምህርት፣ ስልጠና፣ ፈጠራ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ለውጥ ማስመዝገብ ጀምራለች፤ ይህ በመላ አህጉሪቱ መለመድ አለበትም " ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ወጣቶች ልማትና ልህቀት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ወጣት ፉአድ ገና ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላም እድገትና ልማት የወጣቶች ትብብርና አካታችነት መኖር ግዴታ ነው ይላል፡፡

የወጣቶችን አቅም ለመገንባት ደግሞ መተባበርና በፈጠራ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች አቅምን መገንባት የሚያስችል ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም