የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት ውጤት የሆኑ እሴቶችን እንዲጠቀምባቸው እየተሰራ ነው

142

ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት ውጤት የሆኑ ጠንካራ እሴቶችን እንዲጠቀምባቸው የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

የገዳ ስርዓት አካልና የኦሮሞ ሕዝብ ጥንታዊ የመረዳጃ ሥርዓት የሆነው 'ቡሳ ጎኖፋ' የተሰኘ ንቅናቄ በይፋ ሲጀመር የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ እንደገለጹት፤ የኦሮሞን ሕዝብ የሚያጠናክሩና የሚጠቅሙ እሴቶች ሕጋዊነት ኖሯቸው እንዲተገበሩ በአዋጅ እየጸደቁ ነው።

የዜግነት አገግልግሎት ወይም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አዋጅ ጸድቆ እየተተገበረ እንደሆነ በአብነት አንስተው፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባለፉት ሰባትና ስምንት ወራት ብቻ ወደ 3 ሺህ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሕዝቡን ችግር ማቃለል የሚችል በቢሊዬን ብር የሚገመት ሥራ መሠራት እንደተቻለም አንስተዋል።

ሌላው የገዳ ሥርዓት እሴት የሆነው ባህላዊ ፍርድ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአዋጅ ሕጋዊ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በክልሉ ማቋቋም የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

በዚህም በርካታ ጥቅሞች እየተገኙና ሰላም የሚጠበቅበት ሥርዓት እየተተገበረ መሆኑን ተናግረው፤ 'ቡሳ ጎኖፋ' የተሰኘው ጥንታዊ የሕዝቡ መረዳጃና ማቋቋሚያ ሥርዓትም ሕጋዊነት ባለው መልኩ ይተገበራል ብለዋል።

'ቡሳ ጎኖፋ' የኦሮሞ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ሰው ሰራሽም ይሁን ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲያጋጥሙት እርስ በርስ የሚረዳዳበት ሥርዓት መሆኑን ጠቅሰዋል።

'ቡሳ ጎኖፋ' በአዋጅ ተቋቁሞ ቢሮ ተደራጅቶለት እየተመራ መሆኑን የጠቀሱት የ'ቡሳ ጎኖፋ' ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ከድር፤ ሥርዓቱ በተጠናከረ መልኩ ሲተገበር ሕዝቡ ሌሎችን ሳይጠብቅ በራሱ መንገድ ከችግሩ እንዲወጣ የሚያደርግ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

'ቡሳ ጎኖፋ' በዋናነት ከመንግስት ከሚመደብለት በጀት በተጨማሪ ከአባላት መዋጮና ከሌሎች አካላት ድጋፍ የሚደጎም መሆኑንም አንስተዋል።

በንቅናቄ ማስጀመሪያ ሥርዓቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤን ጨምሮ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የባንክ መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም