በሰቆጣ ከተማ ለአሸባሪው ሕወሓት ሊተላለፍ የነበረ አምስት ሚሊዮን ብር ተያዘ

98

ሰቆጣ፤ ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ ለአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ሊተላለፍ የነበረ አምስት ሚሊዮን ብር መያዙን የአስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

“ከአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ሰርጎ ገቦችን” በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሸጌ መንግስቴ ከግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተደረገ የተቀናጀ ጥረትም ለሕወሓት የሽብር ቡድን ሊደርስ የነበረ አምስት ሚሊዮን ብር መያዙን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ገንዘቡን ለሽብር ቡድኑ ሊያደርሱ የነበሩ 20 ተጠርጣሪዎች በጸጥታ ኃይሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አመልክተዋል።

በሌላ በኩል “ከአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 20 ሰርጎ ገቦች” በከተማ አስተዳደሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ፖሊስ በተያዙት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም ነው የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ያስረዱት።

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ግብረ ሃይል ከግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የሰውና ተሽከርካሪ የሰዓት እላፊ እገዳን ጨምሮ የተለያዩ ገደቦችን መጣሉ ይታወቃል።

ከትናንት በስቲያ በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ አስተዳደር ለአሸባሪው ሕወሓት ሊተላለፍ የነበረ ሶስት ሚሊዮን ብር ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የዞኑ አስተዳደርና ፀጥታ መምሪያ መግለጹ የሚታወስ ነው።