አሸባሪው ሕወሓት በግዳጅ ዜጎችን ለውትድርና በመመልመልና እርዳታን ለእኩይ አላማ በመጠቀም ተግባሩ እንዲጠየቅ ጥሪ ቀረበ

90

ግንቦት 17/2014/ኢዜአ/ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ሕወሓት በግዳጅ ዜጎችን ለውትድርና የመመልመልና እርዳታን ለእኩይ አላማ ለማዋል ተግባሩ ተጠያቂ ሊያደርገው እንደሚገባ ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው ”አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ (ኤፓክ)” የተሰኘው የሲቪክ ተቋም አስገነዘበ።

የኤፓክ ሊቀመንበር አቶ መስፍን ተገኑ ለተመድ ዋና ጸሐፊ የሕጻናትና የትጥቅ ግጭት ልዩ ተወካይ ቨርጂኒያ ጋምባ በጻፉት ደብዳቤ ሕወሓት ዜጎችን በግዳጅ መሳሪያ እያስታጠቀ መሆኑን ሮይተርስና የባልሲሊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጌራልድ ባደረጉት ምርምራ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ ምርመራዎች ልጆቻችሁን ለውትድርና ካልሰጣችሁ ቤተቦቻችሁን እናስራለን በሚል ማስፈራሪያ ንጹሃን ዜጎች በግዳጅ ቡድኑን እየተቀላቀሉ መሆኑን ካነጋገሯቸው ሰዎች መረጃ እንዳገኙ አመልክተዋል።

May be an image of text

ፕሮፌሰር አን እና ሮይተርስ በሕወሓት በግዳጅ ወታደር የሆኑ ሕጻናትን ማነጋገራቸውንና እ.አ.አ በ2021 የኒው ዮርክ ታይምስ የፎቶ ጋዜጠኛ ካናዳዊው ፊንባር ኦሬይሊ በዚሁ ተመሳሳይ ጉዳይ በምስል የተደገፈ መረጃ ማውጣቱን ተናግረዋል።

ሮይተርስ “ከዚህ ቀደም በጦርነቱ የተሳተፉ የትግራይ ተወላጆች በድጋሚ የመዋጋት ፍላጎት እንዳሌላቸው ነግረውኛል” ሲል መግለጹን የተናገሩት አቶ መስፍን ሕጻናት ዳግም ተገደው ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ለልዩ ተወካይዋ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል።

ሕወሓት ለዳግም ጦርነት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ ያሉት ሊቀ-መንበሩ፤ ቡድኑ በሚያሳዝን ሁኔታ ሕጻናትን ለጦርነቱ መጠቀሙ አይቀርም ብለዋል።

የባልሲሊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጌራልድ በጥናቷ “የትኛውንም ያህል መጠን ያለው እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ቢገባ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሕወሓት መሪዎች፣ ከሕወሓት ጋር ለተሳሰሩ ነጋዴዎች (እህልና ዘይት በሱቃቸው ይሸጣሉ) እና የቡድኑ ታጣቂዎች” እንደሆኑ ማረጋገጧን አመልክተዋል።

“የእርዳታ ድርጅቶች እንዴት እርዳታ ይሰራጫል? በሚለው ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ድምጽ የላቸውም” ስትል ዳይሬክተሯ መግለጿን ነው አቶ መስፈን በደብዳቤው ላይ ያመለከቱት።

የሕወሓት መሪዎች ለእርዳታ ቅድሚያ የሚሰጡት ለጦርነት ልጆቻቸውን ለሰጡ ቤተሰቦች ነው ይህም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩ የትግራይ ሕጻናት ላይ የባሰ ጉዳት እንደሚያስከትል ገልጸዋል።

የተመድ ዋና ጸሐፊ የሕጻናትና የትጥቅ ግጭት ልዩ ተወካይ ቨርጂኒያ ጋምባ የዓለም መንግስታትንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ስብሰባ በመጥራት ሕወሓትን በግዳጅ ዜጎችን ለውትድርና የመመልመልና እርዳታን ለእኩይ አላማ ለማዋል ተግባሩ ተጠያቂ እንዲያደርጉት ሊቀ-መንበሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጦርነት በሚፈጥረው ጠባሳ ሕጻናት ሲጎዱ ማየትና መፍቀድ የለበትም ብለዋል።

የፌዴራል መንግስት የሰብዓዊ ተኩስ ማቆምና እስረኞችን መልቀቅ ጨምሮ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችሉ ሌሎች እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም ሕወሓት ሰላምና እርቅን ለማምጣት የሚመጥን ምላሽ እየሰጠ አይደለም ያሉት አቶ መስፍን፤ የፈረንሳዩ ዕለታዊ ጋዜጣ ለ ሞንድ “ሕወሓት አሁን በአፋር ክልል ከያዛቸው አካባቢዎች ለቆ አለመውጣቱንና በያዘው ቦታ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው” በሚል ያወጣውን ዘገባ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ተመድ ህጻናት በግዳጅ ለውትድርና እንዳይመለመሉና ሕይወት አድን እርዳታ ከማግኘት እንዳይከለከሉ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል የኤፓክ ሊቀ-መንበር በደብዳቤያቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም