መገናኛ ብዙሃን ለሃገር በቀል እውቀቶች በቂ ሽፋን እየሠጡ አይደለም-የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር

69

ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን ለሃገር በቀል እውቀቶች በቂ ሽፋን እየሠጡ አለመሆኑን የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።


“ልሂቃን፣ሚዲያ እና ሀገር በቀል እውቀቶች ለሰላም ግንባታ ያላቸው ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የባህል ጥናት ጉባኤ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን እያካሄደ ይገኛል።


በጉባኤው ላይ የተገኙት የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ፤የሀገር በቀል ዕውቀትን የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየተሠራ ይገኛል።


ለሀገር ዕድገት እና ለሰላም ግንባታ መሠረት የሆኑት ሀገር በቀል እውቀቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።


የሀገር በቀል ዕውቀት ጠቀሜታን ለማህበረሠቡ ተደራሽ ለማድረግ የመገናኛ ብዙሃን እና የልሂቃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ነገር ግን በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙሃን በኩል ለሃገር በቀል እውቀቶች የሚሰጠው ሽፋን በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል።


ሚኒስትር መሠራያ ቤቱ በልሂቃን የሚሠሩ የምርምር ስራዎችን ጨምሮ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በአግባቡ በመጠበቅና በመሠነድ ለትውልድ እንዲተላለፉ ይሰራል ብለዋል።


የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ማሾ በበኩላቸው ሀገር በቀል እውቀቶች ለሀገር ሰላም የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ አምቦ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ስራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።


የመገናኛ ብዙኃንና የትምህርት ተቋማትም ለሃገር በቀል እውቀቶች መጎልበት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።


ሐገር በቀል ዕውቀቶች ጊዜ ያለፈባቸው ሳይሆኑ ዘመንን የሚሻገሩ ዕውቀቶች በመሆናቸው ሊጠበቁ ይገባል ብለዋል።


በጉባኤው ላይ በሀገር በቀል እውቀቶች ዙሪያ ምርምር ያካሄዱ ምሁራን፣ አባ ገዳዎች፣የህዝብ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️