ሀገርን የሚገነቡ የፈጠራ እጆች

180

                                      (በጣፋጩ ሰለሞን ከጂንካ)

 ወጣት ስብሃት ገብረኢየሱስ ይባላል። ትውልዱና እድገቱ በአርባ ምንጭ ከተማ ነው። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተከታተለው ወጣት ስብሃት፤ በ2004 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስዷል።

የሜካኒካል ምህንድስናን ተምሮ ኢንጅነር መሆን የልጅነት ህልሙ  መሆኑን የሚናገረው ወጣቱ በወቅቱ የ10ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤት አለማምጣቱ ተስፋ እንዲቆርጥ አላደረገውም፤ይልቁነስ በዘርፉ ያገኘውን ዕውቀት ተጠቅሞ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር ህልሙን እውን ለማድረግ ሌሎች አማራጮችን ማማተር ጀመረ እንጅ።

በጋራዥ ውስጥ ተቀጥሮ የመካኒክ ሙያ መቅሰም እንደሚቻል ከጎደኞቹ ያገኘውን  ምክረ-ሀሳብ በመሰነቅ ጉዞውን ወደ ጂንካ ከተማ አደረገ። በከተማዋም የጋራዥ ሥራውን ሀ ብሎ ጀመረ። ለሶስት ዓመታት ከሰራ በኋላም የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአውቶሞቲቭ ሙያ ክህሎት ስልጠና በመጀመሩ እስከ ደረጃ ሶስት በአውቶሞቲቭ እና ኤሌክትሮኒክስ ሲሰተም ትምህርቱን ተከታተለ። በእንጨትና በብረታብረት ሥራም  ተጨማሪ ትምህርቶችን መውሰድ ቻለ።

 “እነዚህን እውቀቶች ከቀሰምኩ በኃላ የመንግስት ስራ አላማተርኩም፤ ስራዎችም ወደኔ እስኪመጡ አልጠበቅኩም” የሚለው ወጣቱ አብረውት ከተማሩ 6 ጓደኞቹ ጋር በማህበር በመደራጀት ወደ ስራ መግባታቸውን ያስታውሳል።

 ከመንግስት በተደረገላቸው የገንዘብ፣የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ድጋፍ በእርሱ ሰብሳቢነት በ2008 ዓ.ም  በ80 ሺህ ብር ካፒታል ”ቤቴል የእንጨትና የብረታብረት ስራዎች ኢንተርፕራይዝ” መመስረቱን የሚናገረው ወጣቱ፤ አሁን ላይ የማህበሩን ካፒታል ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉን አመላክቷል። የማህበሩ አባላት ለሥራ ያላቸው ትጋት፣ የቀሰሟቸውን እውቀቶች ወደ ተግባር መቀየር መቻላቸው  የማህበሩን ስራ ውጤታማ አድርጎታል ብሏል።

ለ10 ስራ አጥ ወጣቶች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር የቻለው ማህበሩ ባሳየው ለውጥና ባስገኘው ካፒታል   በ2010 ዓ.ም ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሸጋግል። ማህበሩ ዛሬ ላይ በጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሙያዊ እገዛ አዳዲስ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የቻለ ሲሆን ከወዳደቁ ብረታ ብረቶች የሰራው የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆኗል። የኤሌክትሪክ ማሽኑ በሰዓት እስከ አምስት ኩንታል መኖ በመፍጨት ከሞላሰስና ከፉሩሽካ ጋር ያዋህዳል። ማሽኑ አድካሚ የሆነውን መኖ የማዘጋጀት ሂደት ከማቅለሉ ባለፈ ይባክኑ የነበሩ ተረፈ ምርቶችንም የሚቀንስ፣  ጊዜና ጉልበትንም  ቆጣቢ  ነው።

በቀጣይ ”በከብት ድለባና በወተት ላሞች እርባታ ስራ ላይ የመሰማራት እቅድ አለን” የሚለው ወጣት ስብሃት፤ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኑ ለዚህ ስራ አጋዥ መሆኑንም ተናግሯል። በሙከራ ደረጃ 14 የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በማምረት ለጂንካ ዩኒቨርስቲ ማቅረባቸውን የገለጸው ወጣቱ በቀጣይም ማሽኑን በብዛት በማምረት በከብት ማድለብ ሥራ  ለተሰማሩ ግለሰቦችና አርሶ አደሮች እናሰራጫለን ብሏል ።

 ዘመናዊ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን ለመስራት በሙከራ ላይ መሆናቸውንም የሚናገረው ወጣት ስብሃት በአንድ ጊዜ  ከብዙ ላሞች ወተት ማለብ የሚችል የወተት ማለቢያ ማሽን ለመስራት በሙከራ ላይ እንደሆኑም ጠቁሟል።

በረጅም  ጊዜ ፀረ-ተባይ መድሃኒቶችን የምትረጭ ሰው አልባ ድሮን የመስራት እቅድ እንዳላቸው ገልጾ፤ መንግስት እገዛ ካደረገላቸው በሶስት አመት ውስጥ ማሳካት እንደሚችሉ ተናግሯል። ”ሌሎች ወጣቶችም በተሰማሩበት የስራ መስክ የራሳቸውን አዳዲስ ፈጠራዎች መፍጠር ቢችሉ የሀገራችንን ዕድገት ማፈጠን በቴክኖሎጂም አቅሟን ማበልፀግ እንችላለን” ባይ ነው ወጣት ስብሀት።

 ” ‘ሀገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩላት ነው የሚባለው’  የሚለው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆን ኦፍ ኬኔዲ ንግግር የህይወቴ መርህ ነው” የሚለው ወጣት ስብሃት እኛም በተለይ ወጣቶች እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁ በማለት ራሳችንን መጠየቅ አለብን ሲል ምክረ ሀሳቡን ሰጥቷል።

ሰሞኑን በጂንካ ፖሌ ቴክኒክ ኮሌጅ የተዘጋጀው የደቡብ ኦሞ ዞን የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የፈጠራ ስራዎችና የቴክኖሎጂዎች አውድ ርዕይ  በዞኑ በፈጠራ ስራ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶችን የፈጠራ ሥራ አስተዋውቋል።

የቱርሚ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ መምህርት ፅዮን መንግስቱ በአውደርዕዩ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ካቀረቡት መካከል ተጠቃሽ ናት።ከፀሀይ ብርሃን ሃይል በማመንጨት በሰዓት 40 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ የምትችል   ከወዳደቁ ብረታ ብረቶች የተሰራች ተሽከርካሪ የፈጠራ ስራዋ ናት። የአውደ ርዕዩ ጎብኝዎች በተገኙበት የተሳካ ሙከራ በማድረግ የፈጠራዋን ውጤት እነሆ ብላለች።

መምህርት ፅዮን በቱርሚ ከተማ ከሚገኘው መኖሪያዋ መነሻዋን በማድረግ የማስተማር ስራዋን ወደ ምታከናውንበት  የቱርሚ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ትጓዛለች። የትራንስፖርት አማራጭ የሌለው የሁለት ኪ.ሜ እርቀት የፀሐዩ ሙቀት ተጨምሮበት ለመምህርት ፅዮን ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

”ችግር ብልሃትን” ይወልዳል እንዲሉ የመንገዱ እርቀትና የፀሐዩ ሙቀት አዲስ ነገር እንድታስብ ምክንያት እንደሆናት ትናገራለች። ”ከባዱን የፀሐይ ሃይል ተጠቅሜ አነስተኛ ታክሲ ብሰራስ” በማለት ራሷን  መጠየቋን ታስታውሳለች። ”ተሽከርካሪዋን በንድፍ አስቀመጥኋት በምናብ የነበረችው ተሽከርካሪ ወደ ወረቀት ብትሰፍርም ወረቀት ላይ የሰፈረው ንድፈ ሀሳብ ህይወት ዘርቶ ለማየት ገንዘብ ያስፈልጋልና ስለ ገንዘብ እጨነቅ ነበር” ብላለች።

”የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ” እንዲሉ መምህርት ፅዮን  ህልሟን እውን ለማድረግ  የምታስተምርበት የቱርሚ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግላት ጥያቄዋን ማቅረቧን ታስታውሳለች። የመምህሯ የፈጠራ ሀሳብ  የአከባቢውን ችግር የሚፈታ መሆኑን የተገነዘበው ኮሌጁ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግላት ቃል ገባ የገባውን ቃልም ተግባራዊ አደረገ።

መምህርት ፅዮን ዛሬ ላይ በአከባቢው የሚገኙ  የወዳደቁ ብረታ ብረቶችን በመጠቀም  ወረቀት ላይ የተሳለችውን ተሽከርካሪ እውን ማድረግ ችላለች። ተሽከርካሪዋ በላይዋ ላይ በተገጠሙ ሶላሮች ሃይል በማመንጨት ሰባት ሰዎችን አሳፍራ በሰዓት 40 ኪሎ ሜትር መጓዝ ትችላለች። ከትራንስፖርት አገልግሎቷ ባሻገር ነዳጅ የማትጠቀም በመሆኗ የአየር ብክለትን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደምትጫወት የፈጠራው ባለቤቷ ገልጻለች።

መምህርት ጽዮን ህልሟ ትልቅ ነው ”በተሻለ ዲዛይን አዳዲስ ሞዴል ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን  በማምረት የአካባቢውን የትራንስፖርት ችግር እቀርፋለሁ” የምትለው የፈጠራ ባለቤቷ፤ ተሽከርካሪዎችን ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ለሀገሬ የማስገኘት ህልም አለኝ ብላለች።

”ሀገር እኛ የምንገነባት እንጂ ግንባታዋ አልቆ የምትሰጠን  ስጦታ አይደለችም” የምትለው መምህርት ጽዮን፤ ወጣቱ ከጠባቂነት አስተሳሰብ በመውጣት አዳዲስ ፈጠራዎችን ሊያፈልቅና በተሰማራበት የሥራ መስክ የሀገር ግንባታውን ሊያግዝ እንደሚገባ ምክረ ሀሳቧን ሰጥታለች።

የቱርሚ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዲን አቶ ሉቃስ ማርቆስ  የንድፈ-ሀሳብ ትምህርቶችን በተግባር ለተማሪዎች ለማስተማር እንደዚህ ያሉ የፈጠራ ስራዎች አጋዥ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በቀጣይም ችግር ፈቺ የሆኑ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ተማሪዎች በማቀናጀትና የክህሎት ስልጠና በመስጠት የሀገርን የብልጽግና ጉዞ ማጎልበት በሚያስችል መልኩ የማብቃትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲፈጥሩ የማመቻቸት ሥራ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን  ቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ስልጠና መምሪያ ሃላፊ አቶ ኦሞ ሹሊ በበኩላቸው የቴክኒክና ሙያ ትምህርቶችን የሚከታተሉ ተማሪዎች የተሻለ የፈጠራ ስራ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ተከታታይና ዘላቂነት ያለው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

”ዛሬ ላይ በሙከራ ደረጃ የሚሰሩት የፈጠራ ስራዎች  ነገ ሀገርን  ወደ ላቀ ከፍታ የሚያሸጋግሩ ናቸው” ያሉት ሃላፊው፤ ለፈጠራ ስራዎች ስኬታማነት ሁሉም አካል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል። በተለይም ወጣቱ ትውልድ ሀገር የመገንባት ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ በሚገጥሙት ተግዳሮቶች ተስፋ ሳይቆርጥ በውስጡ ያለውን እምቅ የፈጠራ ችሎታ ማውጣትና መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው በየትምህርት ተቋማት የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎች   ለሀገር እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን መደገፍ፣ ማበረታታትና ወደ ተሻለ ደረጃ የማሸጋገር ሥራ ሊከናወን እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም በዋናነት  በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚማሩ ተማሪዎችን ለላቀ ፈጠራ ማነሳሳት እንደሚገባ ገልጸዋል።

”የበለፀጉ  ሀገራት መነሻቸው ትናንሽ የፈጠራ ሀሳቦች ናቸው”ያሉት አቶ ንጋቱ፤ሀገር በአጭር ጊዜ ወደ ብልፅግና ጉዞ እንድትሸጋገር የፈጠራ ስራዎችን ማበረታታትና አጎልብቶ ለላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባም አሳስበዋል።