የአፍሪካ አገሮችና ቱርክ እየገጠማቸው ያለውን የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ችግር በጋራ ለመፍታት ይሰራሉ

74


ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ አገሮችና ቱርክ እየገጠማቸው ያለውን የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ችግር በጋራ ለመፍታት በትብብር ለመስራት ቱርክ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።


በቱርክ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀው ለሁለት ቀናት የሚቆየው የቱርክ አፍሪካ ሚዲያ ጉባኤ መድረክ ዛሬ ረፋድ ላይ ጀምሯል።


በመድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የቱርክ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ፋርሁቲን አልቱን እንደተናገሩት፤ እየተባባሰ የመጣውን የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመግታት በትብብር መስራት ያስፈልጋል።


በመሆኑም ቱርክ በዚህ ረገድ ከአፍሪካ አገሮች ጋር በመተባበር ለመስራት ዝግጁነት እንዳላት ጠቁመዋል።


ከዚህም ባለፈ ቱርክ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን ትብብር የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፤ “መድረኩ በጋራ በመወያየት በመፍትሄ ሀሳብ ዙሪያ ለመምከር ይረዳል” ብለዋል።


መካሄድ በጀመረው የቱርክ አፍሪካ ጉባኤ ካሉት 80 የፕሬስ አባላትን መካከል 45 አባላቱ በመድረኩ የተገኙ ሲሆን ከኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በመድረኩ ተገኝተዋል።


የአፍሪካ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራን፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የግልና የመንግስት ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች በመድረኩ መገኘታቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ