ትውልዱን በመልካም እሴት በማነጽ የሠላም ግንባታን ለማሳካት መምህራን ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ

204

ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሁኑ ወቅት በመልካም እሴት የሰለጠነ ትውልድን በማፍራት የሠላም ግንባታን ለማሳካት መምህራን ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ተመለከተ።

የሠላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ጋር በመተባበር "ለሀገራዊ ዘላቂ የሠላም ግንባታ የትምህርት ማኅበረሰብ ሚና" በሚል መሪ ቃል የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ተወካዮች፤ የክልሎች የትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች፣ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ተወካዮችና መምህራን ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ የሠላምና የሀገር ግንባታ ሂደት እውን የሚሆነው በሠለጠነ ማህበረሰብ አማካኝነት ነው ለዚህም መምህራን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል።

በሀገሪቱ ለተከሰቱ ችግሮች አንዱ መንስኤ በትምህርት መስክ መስራት የሚገባንን ያክል ባለመሥራታችን ነው ያሉት አቶ ታዬ፤ በትምህርት ቤቶች ላይ ትውልዱን በመልካም እሴት ለመቅረጽ መስራት ይገባናል ሲሉ አመልክተዋል።

ይህንንም እውን ለማድረግ ትልቁን ድርሻ መምህራን ይወስዳሉ ሲሉ አመልክተው ባለድርሻ አካላትና የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርም በዚህ ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ በበኩላቸው ሠላምን በዘላቂነት ለማስፈን የትምህርቱ ማህበረሰብ ተኪ የሌለው ሚና ይጫወታል ሲሉ ገልጸዋል።

ከታች ጀምሮ ትውልዱን በሰላም ግንባታ ለመቅረጽ መምህራን አቅም በመሆናቸው ይህንን ለመደገፍ እንሰራለን ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ትምህርት በሰላም ግንባታ ሂደት የሚኖረውን ሰፊ አስተዋጽኦ በተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፎች እየቀረቡ ይገኛል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም