በአፋር በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ14 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው

114

ሰመራ፤ ግንቦት 16/ 2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል በክረምት በሚካሄደው የአረንጎዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ14 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን የክልሉ አርብቶ አደር፣ ተፈጥሮ ሃብትና እርሻ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዑስማን መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት  በክልሉ በመጪው የክረምት ወራትና በ2015 ዓ.ም  ለሚካሄደው ክልላዊ የአረንጎዴ አሻራ መርሐ ግብር ዝግጅት እየተደረገ ነው።


በክልል ደረጃ በመርሐ ግብሩ ከ14 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።


''የችግኝ ተከላው የሀገር አቀፉን የችግኝ ተከላ ንቅናቄ መሠረት በማድረግ የሚካሄድ ነው'' ያሉት አቶ ዑስማን   ሥራው የክልሉን የአየር ንብረትና ነባራዊ ሁኔታዎች ታሳቢ በማድረግ ዓመቱን ሙሉ እንደ ሚከናወን አስታውቀዋል።

 በክረምት ወራት 4 ሚሊዮን ችግኝ ለተከላ ምቹ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች የሚተከሉ መሆኑን ጠቁመው፤  ቀሪው  ከ10 ሚሊዮን የሚበልጠው ችግኝ ክረምቱን ተከትሎ ባሉ ምቹ ወራቶች የሚተከል ነው ብለዋል።

ከሚተከሉ ችግኞች ውስጥ ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ለምግብነት ሊውሉ የሚችሉና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።


ቀሪው ከ9 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ችግኝ የክልሉን ስነ ምህዳር የሚጠብቁና ለመድሃኒትና ለእንስሳት መኖነት ሊውሉ የሚችሉ ሀገር በቀል ችግኞች መሆናቸውን አስረድተዋል።
 
የችግኝ ተከላው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚከናወን መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፤ "በዋናነት ምቹ የውሃ አቅርቦትና የአየር ጸባይ ባላቸው አውሲ-ረሱ፣ ገቢ-ረሱ እና ሀሪ-ረሱ ዞኖች ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች ይከናወናል" ብለዋል።

እንደ አቶ ዑስማን ገለጻ በአሁኑ ወቅት ለችግኝ ተከላው የመሬት መረጣና የቁፋሮ ሥራ እየተከናወነ ነው።

መርሐ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግ እንዲቻል በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሰብሳቢነት የሚመራ ዓቢይ ኮሚቴና የተለያዩ የቴክኒክ ኮሜቴዎች ተዋቅረው ወደ ስራ መገባቱን አመልክተዋል።

የፈንቲ-ረሱ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢላል ዳርጌ በበኩላቸው በዞኑ በሚገኙ 5 ወረዳዎች በአረንጎዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ400 ሺህ በላይ ችግኝ ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ በዋናነት የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች ላይ አተኩሮ እንደሚካሄድም ገልጸዋል።
የእዋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ሜኤ በኩላቸው በወረዳው ባለው አንድ የችግኝ ማፍያ ጣቢያ ከ30 ሺህ በላይ ችግኝ የማፍላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ተጨማሪ ችግኝ ለማፍላት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
 
በወረዳው እስከ 65 ሺህ ችግኝ ለመትከል መታቀዱን አመልክተው፤ የችግኝ እጥረት እንዳያጋጥምም ከአጎራባች ክልሎች ጭምር ለማምጣት መታሰቡን አመልክተዋል።

በአፋር ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት በአረንጎዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ22 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ከቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም