የሸኔን የጥፋት ድርጊት ለማስቆም እየተወሰደ ባለው እርምጃ ላይ የሚጠበቅብንን እንወጣለን - የባሌ ዞን ነዋሪዎች

97

ጎባ፣ ግንቦት 16/2014 (ኢዜአ) የአሸባሪውን ሸኔ የጥፋት ድርጊት ለመግታት መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ ላይ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ በኦሮሚያ ክልል የባሌ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ከዞኑ 12 ወረዳዎችና ከጎባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት በሰላምና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡

በጎባ ከተማ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የተሳተፉት የዞኑ ነዋሪዎች በአንዳንድ አካባቢዎች አሸባሪው ሸኔ ንጹሃንን በመግደል ሀብት ንብረት በመዝረፍና በማውደም እኩይ ተግባሩን በህዝብ ላይ እየፈጸመ ይገኛል።

የኦሮሞን ህዝብ መደበቂያ በማድረግ በዞኑ አንዳንድ ወረዳዎች የሚንቀሳቀሰው የሸኔ የጥፋት ቡድን ድርጊት ለማስቆምና ለማጥፋት መንግስት በሚያከናውነው ተግባር ላይ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

ከመድረክ ተሳታዎች መካከል አቶ መስፍን አበራ እንዳሉት አሸባሪው ሸኔ የህዝቡን ሰላም በማወክ የክልሉን እድገት ለማቀጨጭ የሚሰራ ቡድን በመሆኑ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

"የቡድኑ ድርጊት ከህዝቡ ባህልና ወግ ያፈነገጠ የጥፋት ድርጊት መሆኑን በመገንዘባችን መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሀገራዊ አንድነት ለማጠናከር የሚያደርገውን ጥረት እንዲሳካ የድርሻዬን እወጣለሁ" ያሉት አቶ አብዱራህማን ሁሴን ናቸው፡፡

“የሸኔ አባላት ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባና የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትንእንዳያደርግ እንዳይፈጽም እየሰሩ ይገኛሉ” ያሉት የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ሙስጠፋ አህመድ ናቸው።

የአሸባሪው ድርጊት ወደ ወረዳቸው እንዳይገባ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው መንግስት የሚወስደው ህጋዊ እርምጃ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

የጎባ ከተማ ከንቲባ አቶ ተሻለ ዲሳሳ በበኩላቸው መንግስት ፀረ ሰላም ኃይሎችን በማጥፋት የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ተደራጅቶ ከፀጥታ አካላቱ ጋር በመጠበቅ የአሸባሪው ጥፋት ድርጊት ወደ ከተማቸው እንዳይገባ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው ነዋሪው እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል፡፡

"የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅና የጸረ ሰላም ቡድኖችን የጥፋት ተግባር ለማስወገድ ህዝብ ትልቅ ሃይል ነው" ያሉት የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ኃይሌ ናቸው።

በዞኑ የህዝብን አቅም ተጠቅሞ ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን ያወሱት ምክትል አስተዳዳሪው፤ አሁንም ሙሉ በሙሉ ሰላሙን ለማስከበር ህዝቡ ለጸጥታ ሃይሉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አቶ አብረሃም "የባሌ ህዝብ አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር የሸኔን ዕኩይ ድርጊት በማኮላሸት የሰላም አምባሳደርነቱን ማስመስከር አለበት" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም