በዞኑ ባህላዊ የሙግት መፍቻ ስርዓቱ የፍርድ ቤቶችን ጫና እያቃለለ ነው

85

ጎንደር ፣ግንቦት 16/2014(ኢዜአ)  በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባህላዊ የሙግት መፍቻ ስርዓት መተግበሩ የፍርድ ቤቶችን ጫና በማቃለል ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ማገዙን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባጠረ የፍርድ ቀጠሮ የአሰራር ሂደት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ35ሺህ በላይ ለሚሆኑ የክስ መዝገቦች የፍርድ ውሳኔ መስጠት መቻሉም ተመልክቷል፡፡

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ቸርነት ተገኘ ለኢዜአ እንደተናገሩት አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓት ባህላዊውን የሽምግልና ስርአት በማጠናከር ዜጎች በፍትህ ስርዓቱ እምነት እንዲያሳድሩ እያገዘ ነው፡፡

ባለፉት 9 ወራት ከ800 በላይ የክስ መዝገቦች ከመደበኛው የፍርድ ቤት የክርክር ሂደት ውጪ አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓት በሆነው በባህላዊ የሽምግልና ስርዓት እልባት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ዜጎችም የፍትህ ስርዓቱ ባመቻቸው አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓት ተጠቃሚ በመሆን የህግ ጉዳዮቹን ባጠረ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በሆነ የሽምግልና ስርዓት ፍትህ ማግኘት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

ባህላዊ የሙግት መፍቻ ስርዓቱ የፍርድ ቤቶችን የስራ ጫና ማቃለሉን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ተከራካሪ ወገኖችም በሽምግልና ሂደቱ ሙሉ እምነት ማሳደር መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በአማራጭ የሙግት ስርዓቱ ከታዩ የክስ ጉዳዮች መካከልም የገንዘብ ብድር፤ የእርሻ መሬት ወሰንና የባልና ሚስት ክርክሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባለፉት 9 ወራት ከቀረቡለት 41ሺህ 930 የክስ መዝገቦች 35 ሺህ 696 መዝገቦችን  ባጠረ የጊዜ ቀጠሮ ውሳኔ በመስጠት የእቅዱን 85 በመቶ ማሳካት እንደቻለም አቶ ቸርነት አስረድተዋል፡፡

”አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓቱ ከሳሽና ተከሳሽ እኩል አሸናፊ የሚሆኑበት ፍትሃዊ ውሳኔ የሚያስገኝ የህግ ስርዓት ነው” ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ የጠበቆች ማህበር ሊቀ-መንበር አቶ ወርቁ ምስጋናው ናቸው።፡

የኢትዮጵያ የሽምግልና ስርዓት “ዘመን ተሻጋሪ የዳኝነት እሴት ነው” ያሉት ሊቀ-መንበሩ፤ በመሆኑም መሰል አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓቶቹ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ካሳ ዘውዱ በበኩላቸው በገንዘብ ክርክር በመደበኛ ፍርድ ቤት “የመሰረትኩት ክስ በሽምግልና ስርዓት እንዲታይ ተደርጎ አፋጣኝ ፍትህ ማግኘት ችያለሁ” ብለዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የዞኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጨምሮ 24 የሚደርሱ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ይገኛሉ።