የአሸባሪው ህወሓት የዳግም ጦርነት ጥሪ ትውልድን የማጥፋት ዘመቻ ነው – ምሁራን

102

ሀዋሳ፤ ግንቦት 16/2014 (ኢዜአ) ”የአሸባሪው ህወሓት የዳግም የጦርነት ጥሪ ትውልድን የማጥፋት ዘመቻ በመሆኑ ከድርጊቱ ተቆጥቦ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመለስ ህዝቡ ሊያወግዘው ይገባል” ሲሉ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ፡፡

በአለም ላይ የተካሄዱ ጦርነቶች አሸናፊና ተሸናፊ ያልነበራቸው ውጤታቸውም ውድመት፣ኪሳራና፣ በሀገራት ላይ ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለ መሆኑን ምሁራኑ ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው ትምህርት ኮሌጅ የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ወንድሙ አለማየሁ ጦርነት በባህሪው አውዳሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ”ለዚህም ሌላ አካል ሳያስፈልግ እኛ ምስክር ነን” ብለዋል ፡፡

”የአሸባሪው ህወሓት የዳግም ጦርነት ጥሪም ትውልድን የማጥፋት ዘመቻ መሆኑ ግልጽ መሆን አለበት” ያሉት አቶ ወንድሙ በተለይ የትግራይ ህዝብ የአሸባሪውን ህወሓት ድርጊት እንዲያወግዝ ጠይቀዋል።

”ጦርነትን እንደ ጀብድ ለሚያዩና ህዝብን ለማስጨረስ ጦርነትን የሚያጎስሙ መሪ ነን ባዮች ወደልቦናቸው ተመልሰው ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል” ብለዋል።

እንደ ሀገር ችግሮችን በውይይት መፍታት የሚያስችሉ መድረኮች እየተዘጋጁ ባሉበት በአሁን ወቅት ጦርነትን እንደተሻለ አማራጭ ለመጠቀም መሞከር ህዝብን የሚጎዳና ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ መሆኑን አመልክተዋል።

የሽብር ቡድኑን በተለያየ መንገድ የሚደግፉ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራትን ከተሳሳተ መንገዳቸው በመውጣት የሽብር ቡድኑን ጸባጫሪነት ሊያወግዙ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ተመራማሪና የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዳኜ ሽብሩ በበኩላቸው ከቀዝቀዛው ጦርነት ማብቃት ወዲህ በአሸናፊነት የተጠናቀቁ ጦርነቶች አለመኖራቸውን ጠቁመዋል።

በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግሮ ችግሮችን መፍታት እየተቻለ ጦርነትን የመረጠው አሸባሪው ህወሓት ለሁለተኛ ዙር ጦርነት የትግራይን ህዝብ ከህጻን እስከ አዋቂ መመልመሉ ተገቢነት የሌለውና ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የአሸባሪው ህወሐት ትንኮሳ ቢኖርም መንግስት እተከተለ ያለውን የሰላም አማራጭ ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።

ጦርነቶች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንደሚፈጥሩ የገለጹት ደግሞ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ኮሌጅ በትምህርት እቅድና ስራ አመራረ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ገላን ጋጉራ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ የተመዘገቡ የእርስ በርስ ጦርነቶች ለሀገር እድገት ማነቆ ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ጦርነትን ምርጫው ያደረገው አሸባሪው ህወሓት ለሁለተኛ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፤ ይሄም ለትግራይ ህዝብ አለመቆሙን እና  ትውልድን የማጥፋት ዘመቻ ላይ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

በመሆኑ የትግራይ ህዝብ አሸባሪውን ህወሓት ከድርጊቱ ሊያስቆመው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ አንድነት ዋጋ የከፈለው የትግራይ ህዝብ በየጊዜው ልጆቹ በጦርነት እንዲማገዱ እያደረገ ያለውን አሸባሪ ቡድን ሊታገለውና በቃህ ሊለው እንደሚገባ አመልክተው፤ መንግስትም የሰላሙን መንገድ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡