ሀገር የተገነባችበትንና ከፍታዋን ለማረጋገጥ የምትጓዝበትን አቅጣጫዎች ለትውልዱ ማስተማር ይገባል

150

አቅጣጫዎች ለትውልዱ ማስተማር እንደሚገባ አመራሮች፣ መምህራንና ነዋሪዎች ገለጹ፤

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ‹‹ ስለኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች›› በሚል መሪ ሃሳብ ድሬዳዋ አስተዳደር ላለፉት ሶስት ቀናት ለሕዝብ ክፍት ያደረገው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ዛሬ ተጠናቋል።

የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እስከ ሀገራዊ ለውጡ ማግስት ድረስ ያሉትን የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የምጣኔ ኃብታዊ ሁሉን አቀፍ መስተጋብሮችና የዕድል ማዕዘናት የተንፀባረቀበት ነው።

አውደ ርዕዩን የተመለከቱ አመራሮች፣ መምህራንና ነዋሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ሀገር የተገነባችበትን ውጣ ውረዶችና ወደፊት ከፍታዋን ለማረጋገጥ የምትጓዝበትን አቅጣጫዎች ለትውልዱ ማስተማር ይገባል ብለዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፖለቲካ ተመራማሪ አቶ ሱራፌል ጌታሁን እንዳሉት አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ የሚከፈለውን መስዋዕትነትና ያጋጠሙ ውስብስብ ሁነቶች የተንፀባረቀበት ነው።

የፖለቲካ ተመራማሪው አቶ ሱራፌል አክለውም አውደ ርዕዩ "የኢትዮጵያን ሁሉን ገፅታዎች የተመለከትኩበት መፅሐፍ ነው" ብለዋል፡፡

ይህቺ ሀገር በተለያዩ ጊዜያት ፈተናዎችን ስታስተናግድ ነበር፤ ፈተናዎቹ በአንድም በሌላም ህዝባችን ላይ የደረሰውን ችግር ፣ ህዝቡ የከፈለውን መስዕዋትነት ያየንበት ነው ያለው ብለዋል።

አውደ ርዕየ በሀገረ መንግሥት ግንባታው ያጋጠመውን ችግርና ስኬቶችን ያየንበት፣ በመሠረተ-ልማት ግንባታ መሪዎች ህዝቡን በልማት ያሳተፉበትን፣ ሕዝቡ ለሀገሩ መስዕዋትነት የከፈለበት ሁኔታዎች ማየታቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ "መፅሐፍ እንደማንበብ ልትወስደው ትችላለህ" ብለዋል።

ይህን አውደ ርዕይ ትውልዱ እንዲማርበት ማመቻቸት እንደሚገባ መምህር ሱራፌል ጠቅሰው፤ ሀገርን ለማሻገርና ወደ ከፍታዋ ማድረስ የሚቻለው ያሳለፍነውንና ያለንበትን በዚህ መልኩ በመማርና በማስተማር መሆኑን አመልክተዋል።

""ሀገር ሲገነባ ብዙ ተግዳሮቶች አሉ፤ የፖለቲካ ተግዳሮት አለ፤ የኢኮኖሚ ተግዳሮት አለ፤ ማህበራዊ ተግዳሮት አሉ፤ እነዚህን ተቋቁሞ ነው ሀገር መንግስት የምታፀናው" ብለዋል፡፡

ይህ አውደ ርዕይ ያሳየን ነገር ሀገር በቀላሉ የሚፀና አለመሆኑን፤ ሀገር ለማፅናት፣ ልማት ለማረጋገጥ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት፣ ብዙ መስዋዕትነትን እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።

አንድ ሀገር ሊቀጥል ሚችለው ህዝቡ በሚከፍለው ከፍተኛ መስዋዕትነት፣ ተጋድሎ እንዲሁም መሪዎች በሚከፍሉት መስዋዕትነት ጭምር እንደመሆኑ አይተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሣሙኤል ሃላላ በበኩላቸው አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያሳለፈችው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የተረዱበት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ እስከ ለውጡ ማግስት ያሉትን ሁነቶች፣ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን በልጆቿ ደምና አጥንት፣ ዕውቀትና ጥበብ እያሸነፈች የምትሻገር ሀገር መሆኗን በግልፅ የተንፀባረቀበት አስተማሪ ዝግጅት መሆኑን ገልጸዋል።

የመምህር ሱራፌልን ሃሳብ የተጋሩት የድሬዳዋ ነዋሪ ወይዘሮ ፋንቱ አርጋው በበኩላቸው አውደ ርዕዩ "ስለሀገሬ በደንብ እንድረዳ ያደረገኝ በመሆኑ አስደስቶኛል" ብለዋል።

ያለችንን አንድ ሀገር ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እኛ እናቶች ልጆቻችንን ለሀገር ሰላም ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ ማስተማር አለብን ሲሉ በአፅኖት ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው አውደ ርዕዩ የኢትጵያን ሁሉን አቀፍ ገፅታና የህዝብን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምን እንደነበሩ ለማንበብ ለማወቅ የሚያግዙ መጽሐፍትን እንደ ማንበብ የሚቆጠር መሆኑን ተናግረዋል።

የድሬዳዋ ነዋሪ ይህን አውደ ርዕይ እንዲመለከት መደረጉ ታሪክን በአግባቡ ለመረዳትና ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያግዝ በመሆኑ ያኮራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአጭር ደቂቃ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የኢትዮጵያን ውጣ ውረዶች፣ ፈተናዎች፣ የነበሩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ምን እንደሚመስል በርካታ ጉዳዮችን በአጭር ጊዜ እንዲመለከቱ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

ለከተማው ህዝብም ይህ ዕድል መሰጠቱ በአጭር ደቂቃ ብዙ መፅሐፍ አንብቦ የኢትዮጵያን ታሪክ አገላብጦ እንደ መረዳት ሰለሚቆጠር የዚህ ዝግጅት አካል እንደሆን በመደረጉ አደንቃለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም