በዘንድሮው ዓመት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቷል

87

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዘንድሮው ዓመት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።


መርኃ ግብሩ ተግባራዊ መደረጉ በየዓመቱ 92 ሺህ ሄክታር የነበረውን የደን ውድመት መጠን ወደ 32 ሺህ ሄክታር ዝቅ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።


የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ኃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ፤ በዘንድሮ ዓመት በደን፣ በፍራፍሬና በደን ጥምር እርሻ መስኮች ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።


ለመርኃ ግብሩ የችግኝ ማፍላትና ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑ ገልጸው በአሁኑ ሰዓት ከ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።


በመጪው ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም የዘንድሮው ዓመት የአገራዊ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የማስጀመሪያ መርኃ ግብር እንደሚኖርም አመልክተዋል።


በአሁኑ ወቅት ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ክትትልና እንክብካቤ አድርጎ የጽድቀት ምጣኔውን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።


በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበረው የደን ሽፋን በህዝብ ቁጥር፣ በመሬት አጠቃቀም፣ በኢንቨስትመንትና ሌሎች ችግሮች ተመናምኖ እንደነበር ገልጸዋል።


“ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ኃሳብ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ከተጀመረ አንስቶ በኅብረተሰቡ ዘንድ የነበረው ግንዛቤ እየተሻሻለ በመምጣቱ ለውጦች እንዳሉ ጠቁመዋል።


ለአብነትም ከአራት ዓመት በፊት የደን መጨፍጨፍ ምጣኔ በዓመት ከነበረበት 92 ሺህ ሄክታር ወደ 32 ሺህ ሄክታር ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።


በአሁኑ ወቅት እየተተከሉ ያሉ ችግኞትን ለውጤት ማብቃት ኢትዮጵያ ለተለያዩ ሥራዎች በዓመት የምታስገባውን 4 መቶ ሚሊዮን የእንጨት ውጤቶች በአገር ውስጥ ለመተካት ቁልፍ ተግባር ነው ብለዋል።


ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት ምጣኔ 84 በመቶ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር እያሱ ተናግረዋል።


የተተከሉ ችግኞች ሙሉ በሙሉ እንዲጸድቁ ተስማሚ ቦታ ላይ መትከል፣ ባለቤት እንዲኖራቸው ማድረግና የአረንጓዴ አሻራ ሥራን ተቋማዊ ማድረግ በቀጣይ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል።


ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ለጎረቤት አገሮች የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን ለማጋራት ባስቀመጠችው እቅድ ለጅቡቲና ለኤርትራ ችግኝ መላኳን አስታውሰዋል።


የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኃሳብ አመንጭነት “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ኃሳብ ላለፉት ሦስት ዓመታት ተካሂዷል።


በመርኃ ግብሩ ከአርሶ አደር ጀምሮ የከተማ ነዋሪ፣ ተማሪ፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት ነው።


ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ