የበድር ጉባዔ በመጪው ሐምሌ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የበድር ጉባዔ በመጪው ሐምሌ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ግንቦት 16/2014/ኢዜአ/ በድር ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ድርጅት 22ኛ መደበኛ ጉባኤውን በመጪው ሓምሌ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ሊያካሂድ ነው።
ጉባኤው ከሓምሌ 8 እስከ 18/2014 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በጉባኤው 2 ሺህ 500 አባላትና ደጋፊዎቹ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የድርጅቱ መሥራችና በአዲስ አበባ የበድር የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ በሽር መሃመድ በሰጡት መግለጫ፤ በድር ምስረታው በውጭ አገር ቢሆንም በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ ይታወቃል።
ለአብነትም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ውስጥ ያደረገው ተሳትፎ የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
አሁን ደግሞ በመደበኛ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መደረጉ ከአገሪቱ ርቀው የሚገኙ ዜጎች በአገራቸው ሁለንተናዊ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
በጉባኤው የሚታደሙ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ጭምር ይዘው እንደሚመጡ ገልጸው በችግር ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ልማት ዳይሬክተር ነብዩ ሰለሞን በበኩላቸው በድር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአገሪቱን ገፅታ በመገንባት ረገድ ያበረከተው አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቀጣይ ሓምሌ ወር የሚካሄደው የበድር ጉባዔም እነዚህን ሥራዎች ለማጠናከርና ሌሎች ልማታዊ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በድር ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ድርጅት ከተመሰረተ 22 ዓመታትን አስቆጥሯል።