በኦሮሚያ ክልል በተያዘው የመኸር ወቅት 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ይሸፈናል

89

ግንቦት 16/2014/ኢዜአ/ በኦሮሚያ ክልል በተያዘው የመኸር ወቅት 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል በመኸር ወቅት በዘር የመሸፈን የግብርና ስራ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ በይፋ  ተጀመረ።   

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ስራውን በይፋ አስጀምረዋል።

በክልሉ በተያዘው የመኸር ወቅት 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ከተዘጋጀው ማሳ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ በኩታ ገጠም ታርሶ ለዘር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ግብርናን የማዘመን ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው ከ4 ሺህ በላይ ትራክተሮች በእርሻ ስራ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው ብለዋል።

በዘንድሮው ዓመት የገጠመውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመተካት በክልሉ 42 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ኮምፖስት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ተረፈ አራርሳ፤ በዞኑ 613 ሺህ ሄክታር ማሳ በኩታ ገጠም ለመዝራት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የመኸር የዘር ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ በኖኖ ወሪዳ ቢፍቱ ጃለላ ቀበሌ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን በኩታ ገጠም ታርሶ የተዘጋጀ 1 ሺህ 35 ሄክታር መሬት በበቆሎ ዘር ተሸፍኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም