በደቡብ ኦሞ የ17 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ንቅናቄ ተጀመረ

ጂንካ፤ ግንቦት 16/2014 (ኢዜአ)፡ በደቡብ ኦሞ ዞን 17 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን የዞኑ ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የክረምት ወራት  የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዛሬ በዞኑ ባካ ዳውላ አሪ ወረዳ አርክሻ ቀበሌ ተጀምሯል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ በቀለ ሎኮርማ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው የክረምት ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ከ32 ሺህ በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች፣ወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀቶችን ጨምሮ  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ።

በዚህም  ከ17  ሚሊዮን  በላይ  ሀገር በቀል  ዝርያ  ያላቸው  የደን  እና  ኢኮኖሚያዊ  ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ አመልክተዋል።

ለመጥፋት የተቃረቡ እንደ ጥድ፣ ወይራ፣ ዝግባ፣ ዋንዛ ፣ ግራቢላ እና ዋርካ  ሀገር በቀል ዝርያዎች የችግኝ ተከላው አካል ናቸው ብለዋል።

 እንዲሁም ማንጎ፣ ፖፖያ፣ ሙዝና የአቮካዶ የፍራፍሬ ችግኞችን በማልማት  ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ቋሚ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር  ግብ መያዙን አመልክተዋል።

የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ በአርሶ አደር  የእርሻ ማሳ  ዳርቻዎች፣  በመንግሥት  እና በግል ተቋማት፣ በወል መሬቶችና በጥብቅ ደኖች አካባቢ መሆኑን አመልክተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኦሞ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት  ኃላፊ እና የዞኑ የመንግስት ተጠሪ አቶ ተካልኝ ጋሎ በበኩላቸው የዞኑ ህዝብ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባለው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በባካ ዳውላ አሪ ወረዳ አርክሻ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር  አግደው ሻክሚ  በበኩላቸው ቀደም ሲልበአከባቢው የሚገኙ ደኖች ለእርሻ ማስፋፊያ ፣ ለቤት መስሪያና ለማገዶ ለማዋል  በተፈጥሮ ደን ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ የደን ሀብቱ መመናመኑን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት የእርሻ መሬታቸው ለጎርፍ አደጋ እየተጋለጠ እና ለምነቱንም እያጣ  በመሄዱ በሰብል ልማታቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

በመንግሥትና በህዝብ ትብብር በተጀመረው የአረንጓዴ ልማትና የአፈርና ውሃ እቀባ ንቅናቄ  ስራ ተጨባጭ ለውጥ በማየታቸው በየዓመቱ በችግኝ ተከላ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

 በዞኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከተተከሉት 75 ሚሊየን ሀገር በቀል ችግኞች ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው  መጽደቁንና የዞኑ  የደን ሽፋንም 13 በመቶ ከነበረበት ወደ 15 በመቶ ማደጉን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም