ለአሸባሪው ህወሓት ሊተላለፍ የነበረ ገንዘብ ተያዘ

190

ወልዲያ፤ ግንቦት 16/2014 (ኢዜአ)፡ በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ አስተዳደር ለአሸባሪው ህወሓት ሊተላለፍ የነበረ 3 ሚሊዮን ብር ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የዞኑ አስተዳደርና ፀጥታ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ ከፍያለው አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት  ህገ ወጥ ገንዝቡ ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋለው ግንቦት 15/2014 ዓ.ም ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ ነው።

ህገ ወጥ ገንዘቡን  በክፍት ብረት ውስጥ በመደበቅ  በጋማ ከብት በሚሳብ ጋሪ ለሽብር ቡድኑ ለማስተላለፍ ሲሞክሩ በህብረተሰቡ ጥቆማና በጸጥታ ሃይሉ በተደረገ ክትትል  በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን አስታውቀዋል።

ተጠርጣሪዎች ከሌላ አካል ተልከው ገንዘቡን  ለሽብር ቡድኑ ለማስተላለፍ መንቀሳቀሳቸውን  በተጠርጣሪዎች ላይ በተደረገ ምርመራ  ማረጋገጥ መቻሉን አመልክተዋል።

 ምርመራው መቀጠሉን አመልክተው፤ ''ይህ የሚያሳየው በውስጣችን ሆነው የሽብር ቡድንን የሚደግፉ አካላት መኖራቸውን ነው'' ብለዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ መሰል ወንጀሎችን ለጸጥታ አካላት ፈጥኖ በመጠቆም በሀገርና ህዝብ ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም