በኢኮኖሚ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የፈጠራና ቴክኖሎጂ ስራዎችን መደገፍ ይገባል

113

አዳማ፣  ግንቦት 15/2014 (ኢዜአ) በኢኮኖሚ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የፈጠራና ቴክኖሎጂ ስራዎችን መደገፍ እንደሚገባ የስራና ክህሎት ሚነስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አስገነዘቡ።

በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች በልዩ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ተወዳዳረው ላሸነፉ 131 ሰልጣኞችና አሰልጣኞች በአዳማ ከተማ ዛሬ ዕውቅና ተሰጥቷል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በሥነሥርዓቱ ላይ በዘላቂነት በኢኮኖሚ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ለፈጠራና ቴክኖሎጂ ትኩረት መስጠት አለብን ብለዋል ።

የበቃ ሥራ ፈጣሪ የሰው ኃይል ለማፍራት በክህሎት፣ ፈጠራና ቴክኖሎጂ በትኩረት መስራት አለብን ያሉት ሚኒስትሯ በተለይ የልዩ ፈጠራ ሰልጣኞችና አሰልጣኞችን አቅም ማጎልበት እንደሚገባም ተናግሯል።

የኦሮሚያ ክልል ሌሎች ምሳሌ የሚሆን የስራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ፣ ጥናትና ምርምር ላይ እየሰራ ላለው ስራ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተደድር የኦሮሚያ የከተማ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው የስራ ፈጠራ  የሀገራችን ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

አቶ አዲሱ እንዳሉት በፈጠራና ቴክኖሎጂ የበለፀገ የሰው ኃይል መገንባት ካልቻልን የፈለግነውን የብልፅግና ጉዞ ማሳካት አንችልም።

በመሆኑም ከኮሌጆች ባለፈ በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ልዩ ዕውቀት ያላቸውን ተማሪዎች እየደገፍን ነው ብለዋል።

በተለይ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት ባለፈ ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች እንዲማሩ መደረጉንም ገልጿል።

በተለይ የቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች በዕውቀትና ክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ማፍራት እንዲችሉ በወርክሾፖችና ላቦራቶሪዎች የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በፈጠራና ቴክኖሎጂ ተወዳድረው ለዕውቅና የበቁ ሁሉ አካላት በያሉበት ከተሞች ከስንቄ ባንክ ጋር በመሆን የብድር፣ የመስሪያና የምርት መሸጫ ቦታዎችን እንደሚመቻችም አስታውቀዋል።

ልዩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ሰልጣኞችና አሰልጣኞች በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ እየተጉ በመሆናቸው የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርግላቸዋል ብለዋል።

የኦሮሚያ የስራ ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ እድሪስ እንደገለፁት ሙያና ክህሎት፣ ልዩ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራዎች በክልሉ ልማትና ዕድገት ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው እየተሰራ ነው።

የጥልቅ የውሃ ጉድጓድ መቆፈሪያ መሣሪያን እና ነዳጅ ቆጣቢ ተሽከርካሪን ጨምሮ 210 የተለያዩ አይነት የፈጠራ ስራ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ለውድድር መቅረባቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግያ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማትን የሚያጠናክሩ የፈጠራ ስራዎችን በማቅረብ 2ሺ 700 አሰልጣኞችና ሰልጣኞች በውድድሩ መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

በልዩ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ተወዳዳረው ላሸነፉ ሰልጣኞችና አሰልጣኞች የሜዳልያ፣ የዋንጫና የገንዘብ ሽልማት እንደተበረከተላቸው የኢዜአ ሪፖርተር ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም